loading
በኬኒያ የኮቪድ-19 ክትባት የማይከተቡ የመንግስት ሰራተኞች ቅጣት ይጠብቃቸዋል::

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 6፣ 2013  በኬንያ የመንግሥት ሠራተኞች በሙሉ የኮቪድ-19 ክትባት እንዲከተቡ የ13 ቀናት ጊዜ ተሰጣቸው ፡፡ በእነዚህ ቀናት ውስጥ የማይከተቡ የመንግሥት ሠራተኞች የዲሲፕሊን እርምጃ ይጠብቃቸዋል መባሉን አፍሪካ ኒውስ በዘገባው አስነብቧል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ሃላፊው ጆሴፍ ኪንዩዋ አንዳሉት ከሆነ ውሳኔው የተላለፈው በተለይ በመምህራንና በፀጥታ ዘርፍ ውስጥ ባሉ የመንግሥት ሠራተኞች አካባቢ የኮቪድ-19 ክትባት የመከተብ ዝንባሌ ዝቅተኛ በመሆኑ ነው ብለዋል።

አንዳንድ የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራ ለመራቅ ሲሉ ሆን ብለው ክትባት ከመውሰድ ተቆጥበዋል ያሉት ሃላፊው ፤ይህ አዝማሚያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መጥቷል ብለዋል። ሰኞ ዕለት ኬንያ 7 መቶ 45 አዳዲስ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ማግኘቷን ሪፖርት ያደረገች ሲሆን፤ ይህም በሽታው ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በሀገሪቱ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎችን ቁጥር ወደ 212 ሺ 573 ከፍ እንዳደረገው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት መንግሥት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የአስትራ ዜኔካ ክትባቶችን የሰጠ ሲሆን አብዛኛዎቹ የመጀመሪያ ዙር ክትባቶች ናቸው ተብሏል። ኬንያ በአመቱ መጨረሻ 10 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ አልማለች ተብሏል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *