loading
በክልሌ የሚገኝ ቅርስ ያለእውቅናዬ  ፈርሷል የሚለው የወረዳው ጽህፈት ቤት ቅርሱን በመልሶ ግንባታ ወደነበረበት መመለስ ይቻላል እያለ ነው

በክልሌ የሚገኝ ቅርስ ያለእውቅናዬ  ፈርሷል የሚለው የወረዳው ጽህፈት ቤት ቅርሱን በመልሶ ግንባታ ወደነበረበት መመለስ ይቻላል እያለ ነው

 

በአዲስ አበባ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ በየካ ክፍለከተማ ወረዳ አንድ በቋሚ በቅርስነት ከተመዘገቡ ቅርሶች መካከል የልዑል ራስ ካሳ የልጅ ልጅ የሆኑት የደጅአዝማች አምዴ አበራ ካሳ መኖሪያቤት የነበረው ይህ ታሪካዊ ቤት አንዱ ነው፡፡

የአዲስ አበባ የቀድሞ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ሕንጻዎች ማሳያ ነው የተባለው እና የያኔውን የኪነህንፃ ጥበብ እንደሚያስታውስ የሚነገርለት  የደጃዝማች አምዴ አበራ ካሳ መኖሪያ ቤት ከተገነባ ከ90 አመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡

ይህ በባህል እና ቱሪዝም እውቅና ተሰጥቶት በ2007 አ.ም በቅርስነት የተመዘገበው ቤት ከገነተ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ከፍ ብሎ፣ “የራስ ካሳ ሠፈር”  በሚባለው እና በልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ስም በሚጠራው ሰፈር ይገኛል፡፡

በዚሁ ሰፈር የአካባቢው ውበት  እና መገለጫ እንደሆነ የሚነገርለት፣የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ እንደ አይናቸው ብሌን እንደሚሳሱለት በቦታው ተገኝተን ተመልክተናል፡፡

ይህንን ቅርስ ሰሞኑን በቤቶች ኮርፖሬሽን ትዕዛዝ መጥተናል የሚሉ ሰዎች  በከፊል አፍርሰውታል። ለምን?

ነገሩ እንዲህ ነው፡፡

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቤቱን አፍርሶ የመኖሪያ አፓርትመንት ለመገንባት የአፓርትመንት ዲዛይንኑን  ይፋ ካደረገ አመታት አልፈዋል፡፡

ይህን ዲዛይን ይዞ ቤቱን ለማፍረስ ጥረት ሲያደርግም ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡

ከዚህ ቀደምም ሙከራዎች እንዳደረገ ከባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህን የኮርፖሬሽኑን የመኖሪያ አፓርት የመገንባት እቅድ እና የዲዛይኑን ይፋ መደረግ ተከትሎ የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 አስተዳደር እና የየካ ክፍለ ከተማ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የአዲስ አበባ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስነት የተመዘገበውን ይህንን እድሜ ጠገብ ቤት በተመለከተ የፌደራል መሥሪያ ቤቱ ከያዘው  እቅድ እንዲታቀብ በተደጋጋሚ መነገሩ እንደውም መካሰስ ደረጃ ላይ እንደደረሱ በየካክፍለከተማ የወረዳ አንድ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሃላፊዋ ለአርትስ ቲቪ ተናግረዋል።

 

ሃላፊዋ እንደሚሉት በዚህ ዙሪያ ከቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ውይይት ተደርጎ የአፓርትመንት ግንባታው ቤቱን ሳይነካ በሚካሄድበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጎም ቤቱ ቅርስ በመሆኑ እንዳይፈርስ ከመግባባት ተደርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ስምምነት ተጥሶ መኖሪያ ቤቱ እንዲፈረስ ተደርጓል ብለዋል።

 

የአካባቢው ነዋሪዎችም የሰፈሩ ድምቀት የነበረው ቤት መፍረሱ ጥፋት እንደሆነ እና  በመፍረሱ የተሰማቸውን በቁጭት ነግረውናል።

የማፍረስ ድርጊቱ ህገወጥ መሆኑን እንደሚያስቡ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ  ቤቱ ሲፈርስ በቦታው እንደነበሩ እና ከፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ታዘን ነው ብለው ቤቱን ሊያፈርሱ የመጡት ሰዎች የተጠቀሙበት ቡልዶዘር መኪና ሰሌዳ እንኳ የሌለው እንደሆነ ነግረውናል፡፡

ሲያፈርሱ የነበሩት ሰዎችም ከነቡልዶዘሩ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ቢወሰዱም ፖሊስ ግን መልሶ ለቋቸዋል ተብሏል፡፡

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሃላፊዎችን በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግነው ሙከራ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ አልተሳካም ፡፡

ከዚህ በኋላ የቅርሱ እጣ ፈንታ ምን እንደሆነ የጠየቅናቸው ሃላፊዋ የፈረሰው መኖሪያ ቤት በብዛት የተጎዳው ከፊትለፊት በመሆኑ የግንባታ ባለሞያዎች  መጠገን እና ዳግም ወደነበረበት መመለስ እንደሚቻል አረጋግጠዋል ብለዋል ።

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *