loading
በኮፓ አሜሪካ ግማሽ ፍፃሜ ብራዚል ከአርጀንቲና ዛሬ ሌሊት ተጠባቂ ጨዋታ ያደርጋሉ፡፡

የ2019 የኮፓ አሜሪካ ውድድር ግማሽ ፍፃሜ ዙር ላይ የደረሰ ሲሆን ዛሬ ከዕኩለ ሌሊት በኋላ በእኛ ሰዓት አቆጣጠር 9፡30 ሲል በሁለቱ ታላቅ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት አርጀንቲና እና ብራዚል መካከል ይከናወናል፡፡

ጨዋታው ቤሎ ሆሪዞንቴ በሚገነው በእስታዲዮ ሚኔሮ ሲደረግ ደስ ሚል የውድድር ጊዜ እያሳለፈች የምትገኘው አርጀንቲና በብራዚል ድል ልትደረግ እንደምትችል እየተዘገበ ይገኛል፡፡

በኮፓ አሜሪካ 2019 ሩብ ፍፃሜ፤ የውድድሩ አስተናጋጅ ብራዚል በመለያ ፍፁም ቅጣት ምት ፓራጓይን 4 ለ 3 ፤ እንዲሁም አርጀንቲና ቬንዙዌላን 2 ለ 0 ድል በማድረግ ግማሽ ፍፃሜውን ተዋህደዋል፡፡

የአልባሴልስቲዎቹ አምበል ሊዮኔል ሜሲ በውድደሩ በፍፁም ቅጣት ምት አንድ ጎል ብቻ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን የሚጠበቅበትን ያህል የጨዋታ እንቅስቃሴ እያደረገ እንዳለ ከብራዚሉ ጨዋታ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡

የብራዚሉ ተከላካይ ቲያጎ ሲልቫም፤ ሜሲ አሁንም የዓለም ምርጡ ተጫዋች በመሆኑ እና በየትኛው ጊዜ ምን እንደሚያደርግ ስለማይታወቅ በጥንቃቄ እንከታተለዋለን ሲል ተደምጧል፡፡  

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች በኮፓ አሜሪካ ውድድር ከ2007 የፍፃሜ ጨዋታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን ያኔ ሴልካኦ 3 ለ 0 ድል ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

በኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ታሪክ ከባለፉት 45 ውድድሮች አስራ አራቱን በማንሳት ዩሯጓይን የምትከተለው አርጀንቲና ባለፉት አምስት የፍፃሜ ውድድሮች ውስጥ በአራቱ ላይ ተፋላሚ ብትሆንም በአንዱም ግን በለስ አልቀናትም፤

በአጠቃላይ በ14 ፍፃሜ ላይ በተቀናቃኞቿ ዋንጫውን ስትነጠቅ፤ ከ1993 በኋላ ደግሞ ይሄንን ድል ማጣጣም ተስኗታል፡፡

ከ2007 በኋላ ዋንጫውን የማንሳት ዕድል ያልገጠማት ብራዚል በበኳሏ እራሷ በደገሰችው መሰናዶ የበይ ተመልካች ለላለመሆን ከፍፃሜ በፊት በሚደረገው የሱፐር ክላሲኮ የፍፃሜ ጨዋታ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት እያለመች በደጋፊዎቿ ፊት ትፋለማለች፡፡

ምናልባትም ከሀገራቸው ጋር ይሄ የመጨረሻ ውድድራቸው ሊሆን ይችላል የሚባሉት ሊዮኔል ሜሲ እና ኩን አጉዌሮ በሌሊቱ ፍልሚያ የሞት ሽረት ትግል ሊያደርጉ እንደሚችሉ እየተነገረላቸው ይገኛል፡፡

ሌላኛው የግማሽ ፍፃሜ ግጥሚያ ቺሊ እና ፔሩ በፖርቶ አሌግሪ ዕረቡ ሌሊት ይገናኛሉ፡፡        

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *