በደቡብ አፍሪካ በተቀሰቀሰው ሁከት ሳቢያ የሟቾች ቁጥር ከ3 መቶ በላይ መድረሱ ተሰማ፡፡
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 16፣ 2013 በደቡብ አፍሪካ በተቀሰቀሰው ሁከት ሳቢያ የሟቾች ቁጥር ከ3 መቶ በላይ መድረሱ ተሰማ፡፡ ለአንድ ወር ያህል በዘለቀው የደቡብ አፍሪካ ብጥብጥ እስካሁን የ 347 ዜጎችን ህይወት መቅጠፉን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል፡፡ 79 የሚሆኑ ሰዎች በጋውንቴንግ ግዛት 276 ዜጎች ደግሞ ክዋዙሉ-ናታል ግዛት መሞታቸውን ከፕሬዝዳንቱ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ሁከቱ በየዕለቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ወደ ዙማ የትውልድ ስፍራ ክዋዙሉ-ናታል እንዲሁም ጋውንቴንግ ከተሞች በፍጥነት መስፋቱ ተጠቅሷል፡፡ አልጀዚራ በዘገባው እንዳስነበበው እነዚህ አካባቢዎች 50 በመቶ የሚሆነው የደቡብ አፍሪካ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚከናወንባቸው ናቸው ፡፡ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ሁከቱን በቁጥጥር ውስጥ አውለናል ቢሉም በኢኮኖሚው ላይ የደረሰውን ጉዳት ግን በቀላሉ መመለስ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ በክዋዙሉ-ናታል ብቻ 1 ነጥብ 36 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያለው ንብረት ሲወድም 161 የንግድ ሱቆች፣ 11 መጋዘኖች እና 8 ፍብሪካዎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል ተብሏል፡፡
ፖሊስ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው ያላቸውን በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን በተወሰኑት ላይ ክስ መመስረቱን ተናግሯል፡፡