loading
በደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ቃጠሎ ተጠርጥሮ በሽብር ወንጀል የተከሰሰው የጎዳና ተዳዳሪ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2014 ከደቡብ አፍሪካ ፓርላማ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ የተጠረጠረው ግለሰብ ሽብርተኝነትን ጨምሮ ከ6 በላይ ክስ ተመሰረተበት፡፡ ትናንትና ለሁለተኛ ጊዜ ችሎት የቀረበው የ49 ዓመቱ የጎዳና ተዳዳሪ ዜንዳይል ክሪስርማስ ማፊ ከሽብርተኝነት በተጨማሪ በዘረፋና ከባድ የእሳት ቃጠሎ በማስነሳት ወንጀሎች መከሰሱም ተሰምቷል፡፡


የአቃቤ ህግ ቃል አቀባይ ኤሪክ ንታባዛሊላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አቃቤ ህግ በተጠርጣሪው ላይ ተጨማሪ 6 ክሶችን ማደራጀቱን ተናግረዋል፡፡ የተከሳሹ ተከላካይ ጠበቃ ማሊ ምፖፉ በበኩላቸው ደንበኛቸው የአእምሮ ጤና ችግር እንዳለበት በማስረዳት በዋስ እንዲለቀቅ ለችሎቱ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ የጎዳና ተዳዳሪ የሆነው ማፊ በቁጥጥር ስር ከዋለ ጀምሮ በበርካታ ሰዎች ዘንድ ክርክር ተነስቷል ነው የተባለው፡፡


ተከሳሹ ችሎት በቀረበበት ወቅት በፍርድ ቤቱ አቅራቢያ የተሰባሰቡ ሰዎች “ማፊ ንጹህ ነው” ፣ “እሱ ጥፋተኛ አይደለም” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ተቃውሟቸውን ሲገልጹ መታየታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ከተከሳሹ ወገን ሆነው የሚከራከሩ ሰዎች እሱ አንድ ምስኪን የጎዳና ተዳዳሪ ሆኖ ሳለ እንዴት ፓርላማ ውስጥ ገብቶ እሳት የሚያስነሱ ቁሶችን በመለየት ወንጀሉን ፈጸመው የሚሉ ሀሳቦችን ያነሳሉ፡፡ አቃቤ ህግ ተቀጣጣይና ፍንዳታ የሚያስነሱ ቁሳቁሶችና የተዘረፉ እቃዎች፣ እንዲሁም የተለያዩ
ዶክመንቶች በእጁ እንደተገኘበት በማስረጃነት ይዣለሁ ነው የሚለው፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *