በጅማ ከተማ ለሸማቾች የተላለፈ ማሳሰቢያ!
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 21፣ 2013 የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ እና የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆነ ምግቦች በጅማ ከተማ መወገዳቸዉን ባለስልጣኑ አስታወቀ ግምታቸው 260 ሺህ ብር የሆነ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈና የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆነ የምግብ ሸቀጦች መወገዳቸውን የኢትዮጵያ ምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታዉቋል፡፡ የባለስልጣኑ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ጅማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመድሃኒት ባለሙያ ኢንስፔክተር ሚፍታህ ዝናብ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ 86 የምግብ ዓይነቶች ተሰብስበው ተወግደዋል።
የምግብ አይነቶቹ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው እና ገላጭ ጽሁፍ የሌላቸውና የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ ሆኖ በመገኘቱ ተሰብስበው እንዲወገዱ
መደረጉን ተናግረዋል። ከተወገዱት ምግቦች መካከል የተለያዩ እና የታሸጉ ጭማቂዎች፣ ለስላሳ መጠጦች፣ የለውዝ ቅቤ እና ከረሜላዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡ ከታሸጉ ምርቶች በተጨማሪ ማርና ቅቤ ላይ ባዕድ ነገር የሚቀላቅሉ ግለሰቦች ስላሉ በጥንቃቄ መሸመት እንዳለበት ባለሥልጣኑ አሳስቧል።
አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥምም በ8482 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል መጠቆም እንደሚቻል ኢንስፔክተሩ አስታውቀዋል።