loading
በ5 ክልሎች እና በ2 የከተማ አስተዳደሮች ኤች አይ ቪ/ኤድስ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ::

አዲስ አበባ፣የካቲት 12፣ 2013 በ5 ክልሎች እና በ2 የከተማ አስተዳደሮች ኤች አይ ቪ/ኤድስ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ:: በ5 ክልሎች እና በ2 የከተማ አስተዳድሮች ኤች አይ ቪ/ኤድስ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የፌዴራል የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት አስታወቀ። እንደ ሀገር የስርጭት መጠኑ በወረርሽኝ ደረጃ ባይሆንም በጋምቤላ፣ አማራ፣ ሀረሪ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ የከተማ አስተዳደሮች ላይ የስርጭት ምጣኔው ከአንድ በመቶ በላይ በመሆኑ በወረርሽኝ ደረጃ እንደሚገኙ የፌዴራል የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና
መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል በትረ ለኢቲቪ ተናግረዋል።

በሀገር ደረጃ የኤች አይ ቪ/ኤድስ በወረርሽኝ ደረጃ ከፍተኛ የስርጭት መጠን ያለባቸው በጋምቤላ 4.6 በመቶ፣ በአዲስ አበባ 3.4 በመቶ፣ በድሬዳዋ 2.5 በመቶ፣ ሀረሪ 2.4 በመቶ፣ በአፋር 1.4 በመቶ፣ በትግራይ 1.2 በመቶ፣ በአማራ 1.2 በመቶ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ብለዋል አቶ ዳንኤል። በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሰረት አንድ በሽታ ወረርሽኝ ነው የሚባለው የስርጭት ምጣኔው አንድ በመቶ እና ከዚያ በላይ ሲሆን፣ እንደ ሀገር የኤች አይ ቪ/ኤድስ የስርጭት መጠን 0.93 በመቶ ስለሆነ በወረርሽኝ ደረጃ አይደለንም ሲሉ አቶ ዳንኤል ገልጸዋል።

የኤች አይ ቪ ኤድስ በገጠር፣ በከተሞች እንዲሁም በተለያዩ በማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ የተለያየ ዓይነት የስርጭት ምጣኔ እንዳለው ተገልጿል። በማህበረሰብ ደረጃ ከፍተኛ የስርጭት ምጣኔ የሚታይባቸው ሴተኛ አዳሪዎች ሲሆን ቁጥሩም 23 በመቶ ነው ተብሏል። በመቀጠልም፣ ባሎቻቸውን በሞት ያጡ ሴቶች ላይ 19 በመቶ ሆኖ ይታያል ብለዋል አቶ ዳንኤል። የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ ኮንስትራክሽን ሳይት ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች፣ አፍላ ወጣቶች ላይ ከ2
በመቶ በላይ የስርጭት ምጣኔ ያሳያል ሲሉ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።

በከተማ ያለው የስርጭት ምጣኔ 3 በመቶ ሲሆን በገጠር ያለው ደግሞ 0.4 ደርሷል ተብሏል። በተጨማሪም በወንዶች ያለው የስርጭት ምጣኔ ከሴቶች ይልቅ ዝቅ ብሎ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ የኤች አይ ቪ የስርጭት ምጣኔ 61 በመቶ የሚሸፍኑት ሴቶች ሲሆኑ፣ 39 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍኑት ወንዶች እንደሆኑ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል። የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል ዙሪያ ዘርፈ ብዙ ምላሽ የሚጠይቅ ስለሆነ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ የስርጭት ምጣኔው መቀነስ ላይ ውጤታማ መሆን ይቻላል ሲሉ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *