loading
ቢጫ ወባ በወላይታ ዞን በወረርሺኝ መልክ ተከሰተ

አርትስ 28/02/2011

ቢጫ ወባ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን በወረርሺኝ መልክ መከሰቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በአካባቢው በሽታውን መከሰቱን ለማወቅም ከነሐሴ 5/2010 እስከ ጥቅምት 16/2011 ድረስ በተካሄደው ጥናትም በበሽታው የተጠረጠሩ 35 ዜጎች መኖራቸው ተገልጿል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ በምርመራ ያልተረጋገጠ የተወሰኑ ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ መሆኑን ሚኒስቴሩ ለኢቢሲ በላከው መግለጫ ጠቁሟል፡፡

የበሽታውን ወረርሺኝ በአፋጣኝ ለመቆጣጠርም የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮትና የተለያዮ አጋር አካላትን ያሳተፈ አገር አቀፍ የባለሞያዎች ቡድን ተቋቁሞ እንቅስቃሴእየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም መሰረት የበሽታው ቅኝትና የቫይረሱ ተሸካሚ የሆኑ ትንኞች ላይ የመከላከል እና የምርመራ ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል ብሏል መግለጫው፡፡

የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠርና በዞኑ የሚኖሩ ዜጎች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከበሽታው ለመከላከል እንዲችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኝተጠቅሷል፡፡

ኢቢሲ እንደዘገበዉ ከባለፈው ጥቅምት 3 እስከ 10/2010 ዓ.ም በወረርሺኙ ለተጠቁና አጎራባች ቀበሌዎች ክትባት በዘመቻ መልክ እንዲሰጥ መደረጉን መግለጫው አብራርቷል፡፡

በዚህም ክትባቱ ከሚያስፈልጋቸው 31 ሺህ 633 ሰዎች ውስጥ 31 ሺህ 365 የሚሆኑ ነዋሪዎችን መከተብ ተችሏል ነው የተባለው፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *