ባለፉት አምስት ዓመታት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃ መያዙ ተገለፀ
ባለፉት አምስት ዓመታት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ እቃ መያዙ ተገለፀ
ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም ባሉት አምስት ዓመታት ገቢ ኮንትሮባንድ 3.16 ቢሊዮን ብር እንዲሁም 537 ሚሊዮን ብር ወጪ ኮንትሮባንድ መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በአምስት ዓመታት ውስጥ በገቢና በወጪ ኮንትሮባንድ በድምሩ ከ3 ቢሊዮን 697 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችና ኬላዎች መያዛቸውን የኮሚሽኑ የ2011 በጀት ዓመት የ6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት አመላክቷል፡፡
አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ሲጋራና የትንባሆ ውጤቶች፣ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመዋቢያ እቃዎች፣ ምግብና መጠጦች እንዲሁም የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች በአምስት አመቱ ውስጥ በገቢ ኮንትሮባንድ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
ህገ-ወጥ ገንዘብ፣ የቁም እንስሳት፣ ቡና፣ ጫት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎች እንዲሁም ማዕድናት በአምስት ዓመቱ ውስጥ በከፍተኛ መጠን በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ የተያዙ ወጪ ኮንትሮባንድ መሆናቸውንም ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በአማካይ በ12.06 ጭማሪ እያሳየ መጥቶ በ2010 ዓ.ም በተያዙ የገቢ ኮንትሮባድ እቃዎች ላይ የ0.22 በመቶ መጠነኛ ቅናሽ የታየ ቢሆንም ፤ቅናሹ ኮንትሮባንድ ባለመኖሩ ምክንያት የመጣ ሳይሆን በወቅቱ በሀገራችን በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት የመያዝ ዕድላቸው አነስተኛ ሆኖ መሆኑን በሪፖርቱ ላይ ተቀምጧል፡፡
በሌላ በኩል ወጪ ኮንትሮባንድም በየዓመቱ በአማካይ በ28.4 በመቶ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱም በሪፖርቱ ተገልጽዋል፡፡
ምንጭ፤- ገቢዎች ሚኒስቴር