ብራዚል በ24 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ ተባለውን የኮሮናቫይረስ ሞት አስመዘገበች፡፡
አዲስ አበባ ፣ግንቦት 27፣ 2012 ብራዚል በ24 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ ተባለውን የኮሮናቫይረስ ሞት አስመዘገበች፡፡ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ለማንሳት እየተንቀሳቀሰች ያለችው ብራዚል ለሁለት ተከታታይ ቀናት በርካታ ዜጎቿ እንደሞቱባት ተገልጿል፡፡ አልጀዚራ በዘገባው እንዳስነበበው በብራዚል በአንድ ቀን ብቻ 1 ሺህ 349 ሰዎች በኮቪድ 19 ምክንያት ህይዎታቸው ማለፉ ተረጋግጧል፡፡ ብራዚል እስካሁን ከ32 ሺህ 500 በላይ ዜጎቿ የሞቱባት ሲሆን በበሽታው የተያዙት ሰዎች ደግሞ ቁጥራቸው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተሻግሯል፡፡ ይሁን እና በርካታ የሀገሪቱ ግዛቶች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባል ተዘግተው የነበሩ ተቋማትን ለመክፈት እየተጣደፉ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንት ዣየር ቦልሶናሮ ግን አሁንም ከህዝቡ ህይዎት ይልቅ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሲያስቀድሙ ይታያሉ እየተባሉ ይተቻሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ ባደረጉት መግለጫ በሀገሪቱ እየተባባሰ ስለመጣው የሞት መጠን ሲጠየቁ ሞት
የሁሉም ሰው እጣ ፋንታ ነው ማለታቸው ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡