ታራሚዎች ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ለሚዲያ ፍጆታ ከመዋል ባለፈ አለመስተካከሉ ተሰማ
አርትስ 03/ 03/2011
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን ጨምሮ የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ዛሬ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ጉብኝት በማድረግ ከታራሚዎች ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።
በውይይቱ ወቅትም ታራሚዎቹ በፍትህ ስርዓቱ፣ በማረሚያ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችግሮች አሁንም እንዳሉ ተናግረዋል።
ታራሚዎቹ ከፍትህ ስርዓቱ ጋር ተያይዞ ወንጀለኛ ያልሆነን ግለሰብ ለፍርድ የማቅረብና አላግባብ የማሰር እንዲሁም ትክክለኛና አግባብየሆነ ፍትህ ከመስጠት አንጻር ችግሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም ይቅርታ ተደርጎላቸው በማይታወቅ ምክንያት በድጋሚ ወደ ማረሚያ ቤት የገቡ ታራሚዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።
ኤፍቢሲ እንደዘገበዉ በተመሳሳይ ወንጀል የተለያየ የፍርድ ውሳኔ እንደሚሰጥም በውይይታቸው ወቅት ተነስተዋል።
ታራሚዎች ላይ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይም ለሚዲያ ፍጆታ ከመዋል ባለፈ አለመስተካከሉን ጠቅሰው፥ ችግሩ እልባትእንዲያገኝ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም በማረሚያ ቤቱ ውስጥ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግሮች ይስተዋላሉም ነው ያሉት።
እንደ ታራሚዎቹ ገለጻ በተለይም ከጤና አገልግሎት አሰጣጥ እና ከወላጆቻቸው ጋር ማረሚያ ቤት ለገቡ ህጻናት የትምህርት እድልንከማመቻቸት አንጻር ችግሮች ይታያሉ።