loading
ቻይና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን የፀጥታ ፈተናዎችን ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት እንደምትደግፍ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 ቻይና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን የፀጥታ ፈተናዎችን ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት እንደምትደግፍ
ገለጸች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የቻይና ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር ዙ ቢንግ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።


በውይይታቸውም አቶ ደመቀ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት እና ቻይና ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለገብ ድጋፍ አድንቀዋል።
በዚህ ረገድ ቻይና በብዙ መንገድ ያደረገችውን ድጋፍ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ እና በግዛት አንድነትዋ ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን እንድታከሽፍ የረዳችውን ጠቅሰዋል።

ቻይና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአፍሪካን ችግሮች ለመፍታት የአፍሪካን መርህ መሠረት በማድረግ የወሰደችው ገንቢ አቋም እና ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ ድጋፎች ሁሉ የሚደነቁ ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልፀዋል። ቻይና ለአፍሪካ አህጉር ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ያደነቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቻይና አፍሪካ የትብብር ማዕቀፍ የቀረቡትን የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ይሁንታ እንዲሰጣቸው
ጠይቀዋል።


ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ መንግስት የወሰዳቸው አበረታች ውሳኔዎች እና ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል። ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር ዙ ቢንግ በበኩላቸው ቻይና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን የፀጥታ፣ የልማት እና
የአስተዳደር ፈተናዎችን ለመፍታት እና የአንድነት እና ራስን የማሻሻል ጎዳና እንዲከተሉ መደገፍ ትፈልጋለች ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *