ቼልሲ ደረጃውን አሻሽሏል
በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የ35ኛ ሳምንት መርሀግብር የመደምደሚያ ጨዋታ በቼልሲ እና በርንሊ መካከል ስታንፎርድ ብሪጅ ላይ ተካሂዶ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
ሰማያዊዎቹ ቅድሚያ ግብ አስተናግደው ወደ መሪነት ቢመለሱም በመጨረሻም አቻ ሁነዋል፡፡
ጄፍ ሄንድሪክ እንግዳዎቹን ቀዳሚ ሲያደርግ ፈረንሳያዊው ንጎሎ ካንቲ አቻ ሲያደርግ ጎንዛሎ ሂግዌን ገራሚ ጎል አስቆጥሮ ቼልሲዎችን ወደ መሪነት አሸጋግሯል፡፡ አሽሊ ባርንስ የሲን ዳይቹን ቡድን አቻ አድርጓል፡፡
በጨዋታው አራት ጎሎች በ24 ደቂቃዎች ውስጥ ቢቆጠሩም ከዚያ በኋላ ባለው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ግብ ሳይስተናግድ በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡
ቼልሲ ማሸነፍ ቢችል ኑሮ ደረጃውን ወደ ሶስተኛ ማሳደግ የሚችል ቢሆንም ይሄንን ሳያሳካ ቀርቷል፡፡ አሁን ላይ ሰማያዊዎቹ ከቶተንሃም ጋር ዕኩል 67 ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ አንሰው አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ዛሬ ሁለት ተስተካካይ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ሲደረጉ ፤ በተመሳሳይ ምሽት 3፡ 45 ይካሄዳሉ፡፡
የማውሪሲዮ ፖቼቲኖው ቶተንሃም ሆተስፐር በአዲሱ ስታዲየም ብራይተንን ያስተናግዳል፡፡ ስፐርሶች ደረጃቸውን ለማስጠበቅ ፤ ብራይተኖች ደግሞ ከወረጅ ቀጠና ስጋት ለመራቅ ብርቱ ትግል ይኖራቸዋል፡፡
ዋትፎርድ ደግሞ ቪካሬጅ ሮድ ላይ ከሊጉ የመውረድ ስጋት ያለበትን ሳውዛምፕተንን ይገጥማል፡፡