አልጄሪያዊያን የሂራክ አመፅ ንቅናቄ ብለው የሚጠሩትን የተቃውሞ ሰልፍ ለመዘከር አደባባይ ወጥተዋል፡፡
አዲስ አበባ፣የካቲት 10፣ 2013 አልጄሪያዊያን የሂራክ አመፅ ንቅናቄ ብለው የሚጠሩትን የተቃውሞ ሰልፍ ለመዘከር አደባባይ ወጥተዋል፡፡ የሂራክ ንቅናቄ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣር በ2019 ፕሬዚዳንት አብደልአዚዝ ቡተፍሊካን ከስልጣን ያስወገዱበት የተቃውሞ ሰልፍ ነው፡፡ ሰልፈኞቹ የኮሮናቫይረስ ሳያስፈራቸውና በአደባባይ በሰባሰብን የሚከለክለውን ህግ ወደጎን በመተው ነው እለቱን እያሰቡ ሌላ ጥያቄ ያነሱበት፡፡
አልጄሪያዊያኑ ያኔ ባነሱት ተቃውሞ ለሁለት አስርት ዓመታት ሀገሪቱን የመሩት ቡተፍላካ ከስልጣን ይውረዱ የሚል ጥያቄ አንግበው ነበር የተነሱት፤ እሱም ተሳክቶላቸዋል፡፡ በዚህኛው ሰልፍ ደግሞ የሲቪል አስተዳደር እንጂ ወታደራዊ ገዢ አልፈልግም፣ ወንበዴው ስልጣኑን ይልቀቅ የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል ነው የተባለው፡፡ አልጀዚራ እንደዘገበው ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰልፈኞች ኬራታ በተባለችው ከተማ ተሰባስበው በአብደልመጅድ ቲቡኔ መንግስት ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
ጥያቄያችን የሥርዓት እንጅ የግለሰብ ለውጥ አይደለም የሚሉት ሰልፈኞቹ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች በሙሉ ተወግደው አዲስ ስርዓት እንዲመጣ ይፈልጋሉ፡፡ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት ለውጥ አራማጆች የአመፅ እንቅስቃሴው ግልፅ ዓላማ ያለውና ለውጥ እስኪመጣ የማይቆም አብዮት ነው በማለት ገልፀዋል፡፡