አዲስ አበባ በይፋ የውሃ ፈረቃ ውስጥ ገባች
አርትስ 05/02/2011
የአዲስ አበባ የውሃ ፍላጎት በየቀኑ ከሚመረተው የውሃ መጠን በመብለጡ ከተማዋ በይፋ የውሃ ፈረቃ አሰራር ውስጥ መግባቷ ተገለጸ።
በፈረቃ በአሰራሩ መሰረት አንድ አካባቢ በሳምንት ውስጥ ውሃ የሚያገኘው ለሶስት ቀናት ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን እንዳስታወቀው በየቀኑ በሚያመርተው ውኃና በነዋሪው ፍላጎት መካከል ከፍተኛ ልዩነት መፈጠሩ ውሃ በፈረቃ እንዲያዳርስ አስገድዶታል።
የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ እንዳሉት በእጥረቱ ሳቢያ ቢያንስ በ12 እና በ24 ሰዓት ልዩነት ውኃ ያገኙ የነበሩ አካባቢዎች እስከ አሥራ ሶስት ቀናት ድረስ በውሃ እጦት እየተቸገሩ ነው።
ይህንን ችግር ለማቃለል በአንድ አካባቢ ቢያንስ በሳምንት ሶስት ቀን ውሃ በፈረቃ እንዲዳረስ እናደርጋለን ብለዋል ዋና ስራ አስኪያጁ።
ፈረቃው የአጭር ጊዜ ዕቅድ ቢሆንም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመሩ የውሃ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየሰራን ነው ብለዋል።
ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት ውሃ የማምረት አቅሙ በቀን 525 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ቢሆንም ከተማው የሚፈልገው የውኃ መጠን ግን በቀን እስከ አንድ ሚሊዮን ሜትር ኩዩብ ይደርሳል ።