አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ 551 ለሚሆኑ የፌዴራል ታራሚዎች ይቅርታ ተደረገ::
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 4፣ 2012 አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ 551 ለሚሆኑ የፌዴራል ታራሚዎች ይቅርታ ተደረገ:: የ2013 ዓ.ም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በፌዴራል፣ በክልልና በመከላከያ ወታደራዊ ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ የፌዴራል ታራሚዎች በተለያዩ መስፈርቶች መነሻ ለ551 ታራሚዎ ይቅርታ ተደረገ ።
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የይቅርታና ምህረት ቦርድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘለቀ ዳላሎ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቁት፥ በፌዴራል ማራሚያ ቤቶች፣ በመከላከያ ወታደራዊ ማረሚያ ቤት እና በተለያዩ ክልሎች ማረሚያ ቤቶች ለሚገኙ የፌዴራል ታራሚዎች የይቅርታ ቦርድ ያቀረበውን ማስረጃ መርምሮ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ መሰረት ፕሬዚዳንቷ የውሳኔ ሀሳቡን ተቀብለው በማጽደቅ ታራሚዎቹ የይቅርታው ታጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በዚህ መሰረትም 1ኛ ደረጃ በይቅርታ አሰጣጥና አፈፃፀም አዋጅ ቁጥር 840/2006 እና አዋጁን ለማስፈፀም በወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2007 በተቀመጡ መደበኛ መስፈርቶች ነው።
ይህም አንድ ታራሚ ከተፈረደበት ፍርድ አንድ ሶስተኛውን መጨረሱ፣ እርቅ በሚጠይቁ (እንደ ግድያ፣ አካል ጉዳት በመሳሰሉ) ጉዳዮች እርቅ መፈፀሙ ሲረጋገጥ እንዲሁም የፈፀመው ይቅርታው መሰጠቱ ለህዝብ፣ ለመንግስትና ለታራሚዉ የሚጠቅም መሆኑ ተረጋግጦ በድምሩ በመደበኛ መስፈርት 293 ታራሚዎች የይቅርታው ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
በሌላ በኩል 2ኛ ደረጃ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማረሚያ ቤቶች ቢከሰት ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ ከ3 ዓመት በታች የተፈረደባቸው፣ በአመክሮ ሊፈቱ ከአንድ ዓመት በታች የሚቀራቸውንና ህፃናት የያዙ እንዲሁም ነፍሰጡር የሆኑ ሴቶችን በመጋቢት ወር 5 ሺህ የሚሆኑ ታራሚዎችን የይቅርታው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን በወቅቱ በመስፈርቱ የሚካተቱ ቢሆኑም በመረጃ አያያዝ ችግር ምክንያት ያልቀረቡ 128 ታራሚዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል ነው የተባለው፡፡
በሶስተኛ 3ኛ ደረጃ ኮቪድ-19 ተጓዳኝ ህመም ባለባቸው ሰዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ ለቫይረሱ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ ታራሚዎችን በመመልመል የፈፀሙት ወንጀል የህዝብ፣የመንግስትንና የራሱን የታራሚውን ጥቅም የማይጎዳ መሆኑ ተረጋግጦ 113 ታራሚዎች የይቅርታው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓልነው ያሉት አቶ ዘለቀ ፡፡
በተመሳሳይ በ4 ደረጃ ኮቪድ-19 በዕድሜ በገፉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል በመሆኑ ይህንን ጉዳት ለመቀነስ ዕድሜያቸው ከ55 በላይ የሆኑ ሴቶችንና ከ65 በላይ የሆኑ ወንዶችን በድምሩ 17 ታራሚዎች የይቅርታው ተጠቃሚ ተደርገዋል፡፡
እንደ አቶ ዘለቀ ገለጻ በአጠቃላይ በአራቱም መስፈርቶች የ911 ታራሚዎች የይቅርታ ጥያቄ የቀረበ ቢሆንም ከወንጀሉ አፈፃፀም፣ ወንጀሉ በህዝብና መንግስት ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት አንፃር እና ታራሚው በፈፀመው ወንጀል መፀፀቱ፣ መታራሙ እና ተበዳዩን መካሱ በአግባቡ ያልተረጋገጠባቸውን ጉዳዮች በመለየት የ360 ታራሚዎች የይቅርታ ጥያቄ በቦርዱ ውድቅ ተደርጓል፡፡
በመሆኑም ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው ታራሚዎች የቀጣይ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን በአግባቡ እየታረሙ እንዲጠብቁ ያሳሰቡ ሲሆን የይቅርታው ተጠቃሚ የሆኑ ታራሚዎች ደግሞ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ የወንጀል አስከፊነትን አውቀው እራሳቸው ወንጀል ከመፈፀም በመታቀብ ሌሎች ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡ በማስተማር መልካም ዜጋ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።