ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ አቋርጠውት የነበረውን ድርድር ለመጀመር ተስማሙ::
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 11፣ 2012ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ አቋርጠውት የነበረውን ድርድር ለመጀመር ተስማሙ:: የሱዳን የውሃ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ረዘም ካለ ውይይት በኋላ ሶስቱም ሀገራት በየራሳቸው ያዘጋጇቸውን የውይይት ሀሳቦች በማስታረቅ ከማክሰኞ ጀምሮ ለመደራደር ተስማምተዋል ብሏል፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው በሳምንቱ መጨረሻ ካርቱም ላይ ተገናኝተው የተዋያዩት የግብፅ እና የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትሮች ቀጣዩ የሶስቱ ሀገራት ድርድር ፍሬያማ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በጋራ በሰጡት መግለጫ በሀሳብ ተቀራርቦ ድርድሩን መቀጠል የሶስቱን
ሀገራት ጥቅምና ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም አብራርተዋል፡፡ ቀደም ሲል በአፍሪካ ህብረት የሚመራው ድርድር የተቋረጠው ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ምክረ ሀሳብ መጀመሪያ በግል እንምከርበት በማለት ግብፅ ሱዳን በመጠየቃቸው ነበር፡፡ ግብፅና ሱዳን የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በሆነችው ደቡብ አፍሪካ አደራዳሪነት የተሻለ ውጤት ላይ መድረስ ይቻላል የሚል ተስፋ አለን ሲሉ መናገራቸውን ዘገባው አክሎ ገልጿል፡፡ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በበኩላቸው በግድቡ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ከድርድር እና ውይይት ውጭ የተሸለ አማራጭ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡