ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ ብትሆንም ወደፊት ብሩህ ተስፋ እንደሚጠብቃት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 10 ፣ 2013 ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ውስጥ ብትሆንም ወደፊት ብሩህ ተስፋ እንደሚጠብቃት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ ተማሪዎቹ ይህን ያሉት የከፍተኛ ትምህርት እና ሳይንስ ሚኒቴር፣ ከፒፕል ቱ ፒፕል፣ ከአፍሪኮም ሲምፖዚየምና ከኢንተርናሽናል ኔትወርክ ፎር ሀየር ኢጁኬሽን ኢን አፍሪካ ጋር ባዘጋጀው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ውይይትና ክርክር መድረክ ላይ ነው፡፡ ውይይቱ በዋናነት ያተኮረው ታላቁ የህዳሴው ግድብና ብሄራዊ ደህንነት፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ደህንነትና የውስጥና የውጭ ስጋቶች እንዲሁም ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይያተኮረ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሀገራችን የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና የተፈጥሮ አደጋዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ከ7 ዩኒቨርሲቲዎች ተወክለው በውይይቱ የተካፈሉ ተማሪዎች የሀገራቸው ጉዳይ እንደሚያገባቸውና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የነሱ ተሳትፎ አስፈላጊ በሚሆንበት መስክ ሁሉ ምንጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
በሀገራችን ጉዳይ ሀላፊነት አለብን ያሉት ተማሪወቹ አሁን የገጠሙንን ሀገራዊ ችግሮች ወደ እድል በመቀየር የተሻለች ሀገርና ብቁ ዜጎችን መፍጠር እንችላለን ብለዋል፡፡ ሀገሪቱን ሊገጥሟት ከሚችሉ የውጭ ስጋቶች መካከል ደግሞ የጎረቤት ሱዳንና የግብፅ ጉዳይ፣ የህዳሴው ግድብ ድርድርን አስመልክቶ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ቅስቀሳወችና የሳይበር ጥቃት ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ተወያዮቹ እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለማስወገድ ያግዛሉ ያሏቸውን የመፍትሄ ሀሳቦችም በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡ መፍትሄ ጠቋሚ ከተባሉት ሀሳቦች መካከልም ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር አለመግባባቶችን በውይይት መፍታት፣ በብሄራዊ ጥቅሞች ዙሪያ ትምርህና ግንዛቤን ማስፋት፣ ግልፅ በሆነ ተግባቦት እርስበርስ መተማመንን መፍጠር፣ የአንድነት መንፈስ ከፍ እንዲል ተግቶ መስራትና የዜጎችን ደህንት መጠበቅ የሚሉት ቀዳሚዎቹ እንደነበሩ ተገልጽዋል፡፡