ከአማካይ ሰራተኞቹ ክፍያ በ1400 እጥፍ የሚበልጠው ስራ አስኪያጅ ደመወዝ…
አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2014 አፕል ኩባንያ ሰራተኞቹ ገቢያችን ከኑሯችን አልመጣጠን አለ የሚል ቅሬታ በሚያሰሙበት ወቅት የዋና ስራ አስፈፃሚው ቲም ኩክ ገቢ በ500 ፐርሰንት ማድረጉ በርካቶቸን እያነጋገረ ነው፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው ባለፈው ዓመት ከደመወዝ ጭማሪ፣ ከጥቅማጥቅም፣ እንዲሁም በጉርሻ መልክ ወደ ኪሳቸው የገባው ገንዘብ ሲሰላ አንድ አማካይ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ ከሚያገኘው በ1,400 እጥፍ ይበልጣል ነው የተባለው፡፡ ይሄ ሁኔታ ያስቆጣቸው የኩባንያው ሰራተኞችም ጠንካራ የሰራተኞች ማህበር አቋቁመው አሰሪ ተቋማቸው በሚፈጸምባቸውን አድልዎ ሊሞግቱት ተዘጋጅተዋል ተብሏል፡፡
ሰራተኞቹን ለዚህ ወሳኔ ያነሳሳቸው የሚያገኙት ደመወዝም ሆነ ጥቅማቅም አሁን ካለው የዋጋ ግሽበት ጋር ሊመጣጠን አለመቻሉ ሲሆን በላይኛውና በታችኛው መዋቅር ያለው የክፍያ መጠን ልዩነት የቅሬታቸው መነሻ መሆኑን ፎርቹን ዶት ኮም ዘግቧል፡፡ አፕል ባለፈው ዓመት 378 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ካፒታሉ 3 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል፤ ይህም ከአሁን ቀደም የትኛውም ኩባንያ አሳክቶት የማያውቀው እድገት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ረብጣ ዶላር አትርፎ ሲያበቃ የሰራተኞቹን የደመወዝና የጥቅማጥቅም መብቶችን ማክበር አልቻለም ተብሎ ይታማል፡፡
በአሜሪካ የሚገኙ የተቋሙ ሰራተኞችም የስታር ባክስ ሰራተኞች እንዴት በማህበር ተደራጅተው ጥቅማቸውን እንዳስከበሩ ልምድ በመውሰድ መብታቸውን የሚያስከብርላቸው ማህበር ለመመስረት እንቅስቀሴ ላይ ናቸው፡፡