ከኦነግ ጋር ለመነጋገር ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ የተጓዙት አሸማጋዮች በሰላም ተመልሰናል አሉ
አርትስ 29/02/2011
ኦነግን ለመሸምገል ወደምዕራብ ኦሮሚያ የተጓዙት አሸማጋዮች ጊዳሚ በሚባለው አካባቢ ከኦሮሞ ነፃነት ጦር መሪ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን ተናግረዋል።
ነቀምትና ጊምቢን ጨምሮ ግጭቶች በተበራከቱባቸው ስፍራዎች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን አግኝተው ማነጋገራቸውን ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ የተናገሩት አሸማጋዮቹ በጉዟቸው ምንም አይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ነው የገለጹት።
ከአሸማጋዮቹ መካከል አንዱ የሆኑት ኢንጂነር መስፍን አበበ ከኦነግ ጋር በምን ጉዳይ እንዳወሩ፤ ምን ስምምነት ላይ እንደደረሱና ቆይታቸው ስኬታማ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ከዜና ምንጩ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሃሳብ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሙሉውን ምላሽ ከመንግስትና ከኦነግ አመራሮች የምትሰሙት ይሆናል ነው ያሉት ኢንጂነር መስፍን።
ውይይታቸውም በአንድ ጊዜ የሚቆም እንዳልሆነና ቀጣይነት እንደሚኖረው ነው የተናገሩት፡፡
ከተጓዦቹ ሌላኛው ሼክ ኀጂ ኢብራኂም እንደሰጡት አስተያየት ከመንግስትና ከኦነግ ወታደሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ከሁለቱም ወገን አንዳንዶች አለቆቻችንን አናግሩ የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ጠቁመዋል።
“በእኛ በኩል የተረዳነው ሁለቱም አካላት ሰላምን እንደሚፈልጉ ነው” ያሉት ሃጂ ኢብራሂም መንግስትና ኦነግ በቅርቡ ተገናኝተው ያወራሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አድማሱ ዳምጠው ለኦቢኤን ቴሌቪዠን በሰጡት መግለጫ ኦነግን ለማነጋገር ወደምዕራብ ኦሮሚያ የተጓዙ ሽማግሌዎች እንዳልተሳካላቸውና ተደብድበው ጉዳት እንደደረሰባቸው መናገራቸው ይታወሳል።
አርትስ ቲቪ አሸማጋዮቹ በሰላም መመለሳቸውን አስመልክቶ የሰጡትን መረጃ በመንተራስ አቶ አድማሱን ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።