ከግንቦት መጨረሻ እስከ ሰኔ ወር መጀመሪያ ባለው ጊዜ ምርጫ ለማካሄድ ዕቅድ ተይዟል ተባለ::
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 ከግንቦት መጨረሻ እስከ ሰኔ ወር መጀመሪያ ባለው ጊዜ ምርጫ ለማካሄድ ዕቅድ ተይዟል ተባለ:: ይህ የተባለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ በሚከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከሲቪክ እና ከመገናኛ ብዙሃን አባላት በመከረበት ወቅት ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት እንደተባለው ከታህሳስ እስከ ጥር ባሉት ጊዜያት የመራጮች ምዝገባ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከጥር የመጀመሪያው ሳምንት እስከ የካቲት አጋማሽ የእጩዎች ምዝገባ እንዲሁም ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ የምረጡኝ ቅሰቀሳ ይጀመራል ብለዋል፡፡ ከምክክር መድረኩ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ እና በምርጫ ሂደት ስለሚወሰዱ የኮቪድ-19 የጥንቃቄ እርምጃዎችን በተመለከተ ከሲቪክ ማህበራት እና ከመገናኛ ብዙሃን አባላት ጋር በመወያየት ግብዓት ይወሰዳል ተብሏል።
በተጨማሪም ሲቪክ ማህበራት አና መገናኛ ብዙሃንን የሚመለከቱ ዋና ዋና የምርጫ እንቅስቃሴዎች እና ዝግጅቶች ላይ ውይይት ተደርጓል። እንደ ወይዘሪት ብርቱካን ገለጻ፣ መድረኩ የተዘጋጀው የሲቪክ ማህበራት እና የመገናኛ ብዙሃን የሚያነሷቸውን ሀሳቦች በመጨረሻ ለሚወጣው የምርጫ ጊዜ ሰለዳ እና የአፈጻጸም
ዕቅድ ላይ በግብዓትነት ለመጠቀም ታስቦ ነው። ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው መመሪያ መሰረት ስራውን ለማከናወን እንዲያስችለው 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መጠየቁን የቦርዱ ሰብሳሲ ወ/ት ብርትኳን ሚዴቅሳ ተናግረዋል።