loading
ወንጀለኞችን የማደንና ለህግ የማቅረቡ ሂደት ገና እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ

አርትስ 07/03/2011
የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ትላንት ማምሻዉን ለአርትስ በላከዉ መግለጫ መንግስት ለህዝቡ
ቃል በገባው መሰረት በሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ሀገርን በመዝረፍና የሀገሪቱን መፃኢ ተስፋ
ለማጨለም የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንዲሁም የሰኔ 16 የቦምብ ፍንዳታን ጨምሮ የተለያዩ
ወንጀሎችን በማቀነባበር የተጠረጠሩትን ተከታትሎ ለህግ ለማቅረብ ተግቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ
ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
መንግስት ይህንን እያደረገ ያለው በአንድ በኩል ባለፉት ዘመናት ህዝቡ በግልፅ ሲጠይቃቸው የነበሩ
የፍትህ ጥያቄዎች በመሆናቸው እና በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ይህንን ለማድረግ ግዴታ ስላለበት
እንደሆነም አስረድተዋል።
“የኢትዮጵያ ህዝብ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የፍትህ ጥያቄ ሲያቀርብ ነበር” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር
ዶክተር አብይ፥ መንግስትም የህዝብ ጥያቄ መመለስ ውዴታው ብቻ ሳይሆን ግዴታውም ነዉ ብለዋል፡፡
በአንድ ሀገር ውስጥ የመንግስት መኖርን የግዴታ ከሚያደርጉት መሰረታዊ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ
ፍትህን ማረጋገጥ እንደሆነም ገልፀዋል።
ፍትህ የሚረጋገጠውም ንጹሃን በኩራት ቀና ብለው የሚሄዱበትና ወንጀለኞች ደግሞ የትም
የማይደበቁበት ስርዓት መፍጠር ስንችል ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ንፁሃን ዜጎች እንጂ ወንጀለኞች በኩራት የሚኖሩባት ሀገር መሆን የለባትም ያሉት ጠቅላይ
ሚኒስትሩ፥ ወንጀል የፈፀሙት እንዲቀጡበት፣ ሊፈፅሙ ያሰቡት እንዲጠነቀቁበት፣ እነርሱን ሊከተሉ
የሚከጅሉት እንዲማሩበት ሲባል ወንጀለኞችን የማደንና ለህግ የማቅረቡ ሂደት ገና ይቀጥላል፤ ተጀመረ
እንጂ አልተፈፀመም፤ ዓላማውም በአራቱም አቅጣጫ ሀገሪቱን ከወንጀለኞች ነፃ ማድረግ መሆኑን
አስታዉቀዋል።
“ወንጀልና ካንሰር አንድ ናቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ካንሰርን በልምምጥ፣
በልመና እና በአማላጅ ማዳን አይቻልም፤ ካንሰርን በዝምታ መመልከትም ሞትን በእያንዳንዷ ቀን
በዝምታ እንደ መጋበዝ ነው ብለዋል በመግለጫቸው።
ካንሰር እንደወንጀለኛ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ስለራሱ ካልሆነ ስላለበት አካልም ሆነ ማንነቱን
ስላአገኘበት የሰውነት ክፍል ፈፅሞ እንደማያስብ አስረድተዋል።ሙስናም እንደዛዉ ነዉ እንታገለዋለን
ብለዋል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *