ውርርድ ለማሸነፍ ቀንድአውጣ የዋጠው አሜሪካዊ ህይወቱ አለፈ
አርትስ 27/02/2011
ሳም ቢላርድ የ27 ዓመት ወጣት ነው። ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ከመኖሪያ ቦታቸው አትክልት ስፍራ ላይ ከጓደኞቹ ጋር ወይን እየጠጣ ሳቅ ጨዋታ ላይ ነበር።
ጓደኞቹ ሁኔታውን ሲያስታውሱ “ልክ እንደትልቅ ሰው ለመሆን ብለን ወይን እየጠጣን ስንዝናና ነበር ይላሉ።
የወጣቱ ሳምን እና የቤተሰቡን ህይወት የለወጠው ነገር የተፈጠረው በዚያች ምሽት ነው።ከጓደኞቹ አንዱ የሆነው ጂሚ ጋልቪን በኋላ ላይ ለ ሆም ኤንድ ዘ ሄራልድጋዜጣ ጉዳዩን ሲተርከው እንዲህ ብሎ ነበር።
ተቀምጠን ወይን እየጠጣንና ተፈጥሮን እያደነቅን ስንስቅ መሸ። ድንገት አንድ ቀንድ አውጣ ከአትክልት ስፍራ ውስጥ ወጥቶ ወደኛ ሲመጣ አየን። ከዚያም ይህንን የሚበላ ማነው የሚል ውርርድ ውስጥ ገባን። ሳም ተነሳና ”እኔ እበላዋለሁ” አለ። ከዚያም የሆነው ሁሉ ሆነ ብሏል።
ሳም ቀንድአውጣውን አንስቶ ዋጠው። ጥቂት ቀናት ቆይቶ ግን እግሮቹ ላይ ከባድ ህመም እንደሚሰማው መናገር ጀመረ። በሃኪሞች ሲመረመርም ብዙ ጊዜ አይጦችን በሚይዘው የሳንባ ትል በሽታ እንደተጠቃ ታወቀ።
የ19 ዓመቱ ወጣት ራሱን ስቶ ለ420 ቀናት በሆስፒታል ቆየ ይላል ዘገባው።ከሰመመን ከነቃ በኋላ ከወገቡ በታች መንቀሳቀስ ሳይችል ለስምንት አመታት የኖረው ሳም በያዝነው ሳምንት ህይወቱ አልፏል።
የሳም እናት ኬቲ ባላርድ ለጋዜጣው ስትናገር ያለፉት ስምንት አመታት በልጄ ህይወት ውስጥ በጣም ከባድ ነበሩ ብላለች ።