ውስጣዊና የውጭ ጫና የበረከተባት ሱዳን የጣለችውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አነሳች፡፡
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 ውስጣዊና የውጭ ጫና የበረከተባት ሱዳን የጣለችውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አነሳች፡፡ ወታደራዊ አስተዳደሩን የሚመሩት ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ከወራት በፊት ተጥሎ የነበረው የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ መነሳቱን ይፋ ሲያደርጉ ከአዋጁ ጋር በተገናኘ የታሰሩ ሰዎች እደሚፈቱም ፍንጭ
ሰጥተዋል ተብሏል፡፡
የአዋጁ መነሳት የተሰማው በሱዳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካይ በሳምንቱ መጨረሻ ለተቃውሞ የወጡ ሰዎች ባፀጥታ ሃይሎች መገደላቸው ቅር እንዳሰኛቸው ከገለጹ በኋላ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በሱዳን የተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ሀገሪቱ ከዓለም ባንክና ከአሜሪካ የሚገኘውን እንዳታገኝ እንቅፋት የፈጠረባት ሲሆን የአዋጁ መነሳት ይህንኑ ጫና ለማቃለል ያለመ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡
ወታደራዊ አስተዳደሩ ስልጣኑን ለሲቪል ባለማስረከቡ ሳቢያ ሱዳን ከዓለም ባንክ ታገኘው የነበረውን የ2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ያጣች ሲሆን ዋሽንግተንም ለመለገስ አስባው የነበረውን 700 ሚሊዮን ዶላር ለጊዜው እንዲቆይ አድርጋለች ሲል አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ከውጫዊው ጫና በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ውጥረት ጄኔራሎቹን ስጋት ውስጥ እዳስገባቸውና በዚህም የመለሳለስ አዝማሚያ ማሳየታቸው ነው የተነገረው፡፡