“ዘላቂ ሰላም የሚገኘው በህዝቡ ያላሳለሰ ጥረትና ትጋት እንዲሁም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በሚኖር መቀናጀት ነው” ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል
በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም የሚገኘው በህዝቡ ያላሳለሰ ጥረትና ትጋት እንዲሁም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በሚኖር መቀናጀትና መደጋገፍ መሆኑን የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል አስገነዘቡ።
በሰሜን እዝና በትግራይ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ የሰላምና የደህንነት ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
የትግራይ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ አመራሮች ጋር የጋራ የሰላምና የደህንነት ኮንፈረንስ ባካሄዱበት ወቅት ርዕሰመስተዳድሩ በክብር እንግድነት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንዳስገነዘቡት የሃገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝን ጨምሮ ህዝባዊ ባህሪን የተላበሰ መሆኑን ተናግረው የተሟላ ግዳጅን በመወጣት ብቃቱ የሀገሪቱ የኩራት ምንጭ ሆኖ መዝለቁንም አስታውሰዋል።
የሰሜን ዕዝ ምክትል ኣዛዥ ሜጀር ጄነራል አማረ ገብሩ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የትግራይ ክልል ህዝብና መንግስት በሀገራችን አስተማማኝ ሰላም ይገኝ ዘንድ ታላቅ ተጋድሎ ያደረገና ከባድ መስዋዕትነት የከፈለ ህዝብ ነው ብለዋል።
በሰራዊቱና በህዝቡ መካከል የነበረውና ያለው ግንኙነት እጅግ መልካምና የሚደነቅ ነው ብለዋል ጄኔራል አማረ።
የትግራይ ክልል ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ኣቶ ተኪኡ መተኩ በበኩላቸው፥ በትግራይ ክልል ለረዥም ጊዜ የቆየው የሰሜን ዕዝ ሰራዊት ከህዝብ ጋር ያለው ማህበራዊ መስተጋብር የሚመሰገን መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ለሚኖረው ሰላምና መረጋጋት ዋነኛ ጉልበት ሆኖ የሚቀጥለው የክልሉ የውስጥ ኣቅምና የህዝቡ ተሳትፎ ነው ያሉት ሃላፊው፥ ለሚፈጠር ማንኛውም ችግር ተወቃሽ የሚሆነውም የክልሉ መንግስት መዋቅር መሆኑን አስገንዝበዋል።
ስለሆነም በክልሉ ለሚፈጠሩ ችግሮች የመከላከያ ሰራዊታችንን የምናስቸግርበት ምንም ኣይነት መነሻ ምክንያት በፊትም ኣልነበረንም አሁንም የለንም ወደፊትም ኣይኖረንም ነው ያሉት ሃላፊው ።
በመድረኩም የኢፌዴሪ የሰሜን እዝ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች እና ከመላው የትግራይ የክልል ዞኖች የተውጣጡ ሃላፊዎች እንዲሁም ከፍተኛ የፀጥታና ደህንነት ቢሮ አመራሮች ተሳትፈዋል።መረጃው የፋና ነው።