loading
የሆንዱራስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት በአደንዛዥ ዕፅ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ።

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 የሆንዱራስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት በአደንዛዥ ዕፅ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ። አሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሁዋን ኦርላንዶ ሄርናንዴዝ በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪነት ክስ ተላልፈው እንዲሰጧት ጥያቄ ካቀረበች ከሰዓታት በኋላ ነው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በፍርድ ቤት የዕስር ትዕዛዝ
የወጣባቸው ተብሏል፡፡ የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ሜልቪን ዱአርቴ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሄርናንዴዝ ላይ የእስር ማዘዣ መውጣቱን አረጋግጠዋል፡፡


ፕሬዚዳንቱ በመኖሪያ ቤታቸው በመቶዎች በሚቆጠሩ ፖሊሶች ተከብበው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መገናኛ ብዙሀኑ ዘግበዋል፡፡ የቀረበባቸውን ክስ በአደንዛዥ እፅ መሪዎች ዘንድ የተከፈተባቸው የበቀል ሴራ ነው በማለት ውድቅ ቢያደርጉም በ24 ሰአት ውስጥ ችሎት ፊት መቅረብ አለባቸው ሲሉ ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።
እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2014 እስካለፈው ጥር ወር ድረስ ሆንዱራስን ያስተዳደሩት ሄርናንዴዝ በግራ ዘመም ፖለቲካ አራማጇ ዢዮማራ ካስትሮ ተተክተው ሀገሪቱ በመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት እየተመራች ነው፡፡


አሜሪካ የቀድሞ አጋሯን ሄርናንዴዝን ባለፈው ወር ከስልጣን ከተነሱ ጀምሮ በጦር መሣሪያ እና በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪነት ክስ ተላልፈው እንዲሰጧት እየሻተች ነው ሲል የሬውተርስ የዜና ወኪል የአሜሪካን ኤምባሲ ሰነድ ጠቅሶ ዘግቧል። ሆንዱራስ ለዓመታት ከደቡብ አሜሪካ ወደ አሜሪካ የሚገቡ አደንዛዥ እፆች ቁልፍ መሸጋገሪያ ሆና የቆየች ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኮኬይን የሚመረትባት ሀገር ሆናለች።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *