loading
የመልሶ ማቋቋም ተግባራት በሰብአዊ መብቶች የሚመሩ መሆን እንዳለባቸዉ ኮሚሽኑ አሳሰበ፡፡

አዲስ አበባ፣ ህዳር 22፣ 2013 የመልሶ ማቋቋም ተግባራት በሰብአዊ መብቶች የሚመሩ መሆን እንዳለባቸዉ ኮሚሽኑ አሳሰበ፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ለአርትስ በላከዉ መግለጫ እንዳስታወቀዉ፤ በቀጣይ በትግራ በሚደረጉ የመልሶ ማቋቋምና መልሶ ግንባታ ተግባራት በፌዴራል መንግሥቱ ሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የመጠበቅ ግዴታ የሚመራ እንዲሆን አሳስቧል፡፡

ኮሚሽኑ በተለይ መንግስት የተጠፋፉ ቤተሰቦች እንዲገናኙና ተገቢው ሰብአዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን የተቋረጡ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ ውሃና ኤሌክትሪክ ኃይልን ጨምሮ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ ሰጪ አካላት አገልግሎት ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ መስራት አለበት ብሏል፡፡ በግጭቱ የተፈናቀሉና የተሰደዱ ሰዎች ወደ መደበኛ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እና የተጠፋፉ ቤተሰቦች እንዲገናኙ የሚያስችል አስፈላጊ የሆነው የሎጂስቲክስና የሰብአዊ እርዳታ መሰረተ ልማት እንዲደራጅ ኮሚሽኑ ጠይቋል::

ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም  የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና ያስከተለውን ሰብአዊ ቀውስ የሚመረምር ገለልተኛና ግልጽ የሆነ አሰራር ከወዲሁ እንዲተገበር፣ ተዓማኒና አካታች የሆኑ የእርቅና የፍትሕ ሂደቶች በጊዜ እንዲደራጁ እፈልጋሉ ብሏል ኮሚሽኑ፡፡ በተጨማሪም ኢሰመኮ በትግራይ ተወላጆች ላይ ብሔርን መሰረት ያደረገ መድሎዎና መገለል ስለመድረሱ የሚቀርቡለት ቅሬታዎች በከፍተኛ ደረጃ እያሳሰበውና እየተከታተለው እንደሚገኝ በላከዉ መግለጫ ጠቅሷል።

ድርጊቱ በተወሰኑ ሰዎች ላይ በተለይም ከሥራ አስገዳጅ የእረፍት ጊዜ በማስወሰድ እና ለሥራ፣ ለህክምናና ለትምህርት  የሚደረጉ ጉዞዎችን  በመከልከል የሚገለጽ መሆኑን ተረድቷል። ኮሚሽኑ ሲያደርግ በነበረው ክትትል መሰረት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት ችግሩ በአፋጣኝ እንደሚቀረፍ  ምላሽ ተሰጥቶኛል ብሏል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *