loading
የመቀሌ ዩኒቨርስቲ በአትሌቲክስና በብስክሌት ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ውድድር ተሳትፈው አንፀባራቂ ድል ላስመዘገቡ ሁለት ሴት ስፖርተኞች የማበረታቻ ሽልማት ትናንት አበረከተ ።

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2013 የመቀሌ ዩኒቨርስቲ በአትሌቲክስና በብስክሌት ስፖርቶች በዓለም አቀፍ ውድድር ተሳትፈው አንፀባራቂ ድል ላስመዘገቡ ሁለት ሴት ስፖርተኞች የማበረታቻ ሽልማት ትናንት አበረከተ ።ዩኒቨርሲቲው ለሴት ስፖርተኞቹ የእውቅና ምስክር ወረቀትና የአንገት ሀብል ሽልማት አበርክቶላቸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሽልማት ካበረከተላቸው ሴት ስፖርተኞች መካከል በቅርቡ በስፔን ቫለንሽያ ከተማ በተካሔደው የአትሌቲክስ ውድድር በ5 ሺህ ሜትር ሩጫ የአለም ክብረ ወሰን የሰበረችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ አንዷ ናት ።ሁለተኛዋ ደግሞ በብስክሌት ስፖርት በቱር ደፍራንስ በመሳተፍ አንፀባራቂ ድል ያገኘችው ብስክሌተኛ እዮሪ ተስፋኦም መሆኗን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል ።

በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የመቐለ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፎቴን አባይ እንደተናገሩት ድሉ ሴቶች ያገኙትን መድረክ በመጠቀም ከኢኮኖሚ ጥገኝነት በመላቀቅ ለአገራችን ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ ማሳያ ነው ብለዋል ።”ሁለቱም ሴት ስፖርተኞች ከራሳቸው አልፈው አገራቸውን በአለም አቀፍ መድረክ ማስጠራት ችለዋል” ያሉት ፕሮፌሰር ፎቴን የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በውጤታቸው ኩራት እንደተሰማው ገልፀዋል ።

ዩኒቨርሲቲው የስፖርት ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች በማከናወን ላይ ይገኛል ያሉት ፕሮፌሰር ፎቴን ሴቶች በስፖርት ዘርፍ ጎልተው እንዲወጡ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

አትሌት ለተሰንበት ግደይ ሽልማቱ ከተረከበች በኋላ በሰጠችው አስተያየት “ዩኒቨርሲቲው በሰጠኝ የእውቅና ሽልማት በጣም ተደስቻለሁ ። ለቀጣይም የበለጠ እንዲሰራ ያግዘኛል” ብላለች ።የብስክሌተኛ እዮሪ ተስፋኦም ክለብ የሆነው የመቐለ 70 እንደርታ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይርጋ ገብረእግዚአብሔር በበኩላቸው መቐለ ዩኒቨርስቲ ያዘጋጀው የእውቅና ሽልማት የስፖርት ዘርፉን ይበልጥ እንዲበረታታ የሚያግዝ ነው። የክልሉ ስፖርት ካለበት ደረጃ ከፍ እንዲል በቅንጅት መስራት እንደሚገባም መልእክተቸውን አስተላልፈዋል። አትሌት ለተሰንበት ግደይ ለ12 አመታት በአገሯ ልጅ በጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የነበረው የ5 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን ማሻሻልዋን የሚታወስ ነው ።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *