የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሕዳሴው ግድብ ለፈጸሙት አኩሪ አገራዊ ተልዕኮ ምስጋና ተቸራቸው:
አዲስ አበባ፣ሐምሌ16፣ 2012የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሕዳሴው ግድብ ለፈጸሙት አኩሪ አገራዊ ተልዕኮ ምስጋና ተቸራቸው::የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ መሰረት ጀምሮ አስካሁን ድረስ ለፈጸሙት አኩሪ አገራዊ ተልዕኮ በመከላከያ ሚኒስቴር ምስጋና ተቸራቸው። ሚኒስቴሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግደብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሃመድ ተሰማ ለኢዜአ በላኩት መግለጫ ግድቡ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ዜጎች፣ ከህጻናት እስከ ዕድሜ ባለጸጎች የገንዘብና ሞራል ድጋፍ እየተገነባ ያለ ነው።
የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ንቁ ተሳትፎ የታየበት ትልቅ አገራዊ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል።የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትም ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ክብርና ለህዝብ ሰላም እስከ ህሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል በፍጹም አገራዊ ስሜት መሰለፋቸውን አውስተዋል።ከግድቡ መሰረት ጀምሮ የመጀመሪያው ምዕራፍ ውሃ ሙሌት እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ለፈታኝ የአየር ጸባይ ሳይበገሩና ዐይኖቻቸውን ከግድቡ ሳይነቅሉ አኩሪ ታሪክ ለሠሩ የሠራዊት አባላት ያላቸውን ምስጋናም አቅርበዋል።ከዚህ ባለፈ የሠራዊቱ አባላት ከአነስተኛ ደመወዛቸው ቦንድ በመግዛት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ተግባራዊ የጀግንነት ገድል መፈጸማቸውን ተናግረዋል።