loading
የመካነ ቅርሶች ጉብኝት በኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት አስተባባሪነት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ።

አዲስ አበባ፣የካቲት 5፣ 2013 የመካነ ቅርሶች ጉብኝት በኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት አስተባባሪነት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ።የኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት በደቡብ እና ምእራብ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለመገናኛ ብዙሀን ያዘጋጀው ለሳምንት የሚዘልቅ ጉብኝት በመካሄድ ላይ ይገኛል። በጉብኝቱ የቅርስና ጥበቃ ባለሙያዎች ፣ የጥናት ባለሙያዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሀን ሙያተኞች እየተሳተፉ ይገኛል። ይህ የኢትዮጵያን የአገር ውስጥ ቱሪዝም ለማበረታት እንዲሁም የቅርስና ጥበቃ አስፈላጊነት ለማስተዋወቅ ታስቦ በተዘጋጀው ጉዞ ባሳለፍናቸው ሁለት ቀናት በመልካቁንጥሬ መካነቅርስ ፣ በጥንታዊቷ አዳዲ ማርያም ውቅር ቤተክርስትያን ፣ በጢያ ትክል ድንጋዮች ጉብኝቶቹ ተደርገዋል።

መልካ ቁንጥሬ ፦ ይህ በላይኛው የአዋሽ ሸለቆ የሚገኘው አስደናቂ ታሪካዊ ስፍራ የተገኘው በ1963 ዓ/ም ደከር በተባለ ግለሰብ አማካይነት እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከ1992 – 1995 ዓ/ም ዣን ሻቫዬ የተሰኘ የምርምር ባለሙያ በርካታ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ጠንካራ የቁፋሮ ምርምሮች ተደርገውበታል። በጥናት ውጤቱም በርካታ ታሪካዊ ስፍራዎችና መረጃዎች ተገኝተውበታል። በጉብኝቱ ወቅት በመካነቅርሱ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ተሰማ እንደተገለፀው በዚህ ስፍራ ላይ የሚደረጉት ጥናቶች ዓላማ አገራችን ኢትዮጵያ እንዲሁም የሰውን ልጅ የድንጋይ ዘመን ታሪክ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማወቅ እና ለመተንተን ነው።
በዚህ አስደናቂ ቦታ ከ2ሺህ በላይ የተለያዩ የድንጋይ መሳሪያዎች ፣ የጉማሬና የእፅዋት ቅሪተአካላቶች የተገኙበት ሲሆን በተጨማሪም በቦታው ላይ ዕድሜው 800ሺህ ዓመት የሚገመት የእንስሳትና የሰው እግር ዳና እንደተገኙበት በጥናት ሙያተኞች ተገልጿል። በመካነቅርሱ የሚደረጉ ጥናቶች አሁንም የቀጠሉ ሲሆን መካነቅርሱ በዩኔስኮ ከተመዘገበ የሳይንስ እና ቱሪዝም መዳረሻ ለአገራችን ምጣኔ ሀብታዊ እና ማህበረሰባዊ እድገት ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችል ተገልጿል ።
የጢያ ትክል ድንጋይ ፦ ሁለተኛ የጉዞ እና የጉብኝት መዳረሻ የነበረው የጢያ ትክል ድንጋዮች ናቸው። በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ በሚገኘው የጢያ ትክል ድንጋይ መካነቅርስ ቅጥር ግቢ 41 ያህል የቁም ትክል ድንጋዮች የሚገኙ ሲሆን ቁመታቸው እስከ 5 ሜትር ድረስ የሚረዝሙ ድንጋዮች ናቸው።
ትክል ድንጋዮቹ በተለያዩ ጥንታዊ ምልክቶች የተዋቡ ሲሆን በዛን ዘመን በአካባቢው የነበሩ ማህበረሰቦች እሴቶችና ፍልስፍናዎችን የሚያመላክቱ መሆናቸውን የስፍራው የጥናት ባለሙያዎች ገልፀዋል።
ይህ የኢትዮጵያ አገራችን ልዩ ሀብት የሆነው ስፍራ በ1972 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት መመዝገቡም ይታወቃል። ይህ ጉብኝት የቀጠለ ሲሆን በቀጣይ ቀናቶች በተለያዩ በደቡብ የአገራችን ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ መካነቅርሶችን ተሳታፊዎች እንደሚጎበኙ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ባዘጋጀውና እየተካሄደ ባለው የታሪካዊ ቅርሶችና የቱሪዝም መዳረሻዎች ጉብኝትን መሰረት ያደረገ ዘጋቢ ፊልም አርትስ ቴሌቭዥን በንድራ የቴሌቭዥን መርሃግብር ላይ በቅርብ ቀን ይዞላችሁ የሚቀርብ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።
         ራፋቶኤል ወርቁ

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *