የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማንኛውም ኃይል ከሩሲያ ግዛት ቅንጣት መሬት ለመውሰድ ቢሞክር፣ “ጥርሱን እናራግፍለታለን” ሲሉ አስጠነቀቁ።
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14፣ 2013 የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማንኛውም ኃይል ከሩሲያ ግዛት ቅንጣት መሬት ለመውሰድ ቢሞክር፣ “ጥርሱን እናራግፍለታለን” ሲሉ አስጠነቀቁ። ፕሬዚዳንቱ ከከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው ጋር ባደረጉት የቪዲዮ ስብሰባ በተናገሩትና በቴሌቪዥን በተላለፈው ንግግራቸው፣ አንዳንድ የውጭ ሃገራት በከርሰ-ምድር ሃብት የበለፀገውን ሳይቤሪያ የተባለውን የሩሲያን ግዛት አስመልክቶ ከሚሰጡት አስተያያት ተነስተው መሆኑን ገልፀዋል።
ከውጭ ሃገራት ተነገሩ የተባሉት ነገሮች በቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማድሌን ኦልብራይት የተባሉ ናቸው የሚሉ አስተያየቶች ቢኖሩም የቀድሞዋ ሚኒስትር አላልኩም በማለት ያስተባብላሉ። “አንዳንዶች ጭራሽ በአደባባይ ሳይቀር ሃገሬ ራሺያ፣ ሳይቤሪያን በመሳሰሉ አካባቢዎቿ የተከማቸው የምድር ሃብት ባለቤት መሆኗ ፍትሃዊ አይደለም የማለት ያህል ደፋር ንግግር ይናገራሉ” ሲሉ ግርምታቸውን ገልፀዋል፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን።
እንደዚህ ዓይነት የኃይለኝነት ቃላትን መጠቀም ለደጋፊዎቻቸውና የመንግሥታቸው መሠረት ለሆኑት ሠራዊቱና የደኅንነት አካላቱን ማነቃቂያ ለማድረግ የሚጠቀሙት የሚመስሉት ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ ማንም ኃይል አገራቸውን ለመውረር ቢሞክር የማያዳግምና ጠንካራ ምት እንደሚጠብቀው አሳስበዋል።
“ሁሉም የሆነ ቦታ ሊነክሰን ወይ ደሞ የሆነ የኛን ነገር ቦጭቆ ለመውሰድ ይመኛል” ያሉት ፕሬዚደንቱ፤ “ይኼንን ለማድረግ የሚሞክሩ ሁሉ ማወቅ ያለባቸው ነገር፣ ጥርሳቸውን አራግፈንላቸው ከዛ በኋላ መናከስ እንዳይችሉ እንደምናደርጋቸው ነው” ካሉ በኋላ “ለዛም ደሞ ዋናው ቁልፍ የመከላከያ ኃይሎቻችንን ማጠናከር ነው” በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል። ፕሬዚዳንት ፑቲን ይህንን አወዛጋቢ አስተያየት የሰጡት፣ እሳቸውና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን
ስብሰባ በመቀመጥ እየተበላሸ የመጣውን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እንዲያሻሽሉ ከየአቅጣጫው ጥሪ በበረከተበት ወቅት ነው።