የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የከሰላውን አስተዳዳሪ ከስልጣናቸው አነሱ::
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2013 የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የከሰላውን አስተዳዳሪ ከስልጣናቸው አነሱ:: ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሀምዶክ ባለፈው ሰኔ ወር የከሰላ ግዛት አስተዳዳሪ አድርገው ሾሟቸውን ሳልህ አማርን ከስልጣናቸው ያወረዷቸው በአካባቢው ከተነሳው የጎሳ ግጭት ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
አማር ለግዛቲቱ የመጀመሪያው የሲቪል አስተዳዳሪ ሆነው ከተሸሙ ጀምሮ ቤጃ ከተባሉት ጎሳዎች ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማቸው ሲሆን ወደ ግዛቲቱ እንዳይገቡ ታግደው ነበር ነው የተባለው፡፡ በዚህም የተነሳ አስተዳዳሪው የተቃውሞ ሰልፉ ከመባባሱ አስቀድሞ ካርቱም ውስጥ ለመቆየት ተገደው እንደነበር አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የቤጃ ጎሳዎች በቅርቡ ጁባ ላይ በተፈረመው የሰላም ስምምነት የኛ ውክልና በበቂ መጠን አልተካተተበትም በማለት ያስነሱት አመፅ በቀይ ባህር የሚገኘው ፖርት ሱዳን ለሶስት ቀናት ያህል እንዲዘጋ ምክንያት ሆኖ መነበር፡፡ ለተቃውሞው መባባስ ከጀርባ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ደጋፊዎች እጅ ሳይኖርበት እንደማይቀር የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡
የሱዳን መንግስት ነፍጥ አንግበው ከሚዋጉ ተቃዋሚዎች ጋር የፈረመው የሰላም ስምምነት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ድጋፍ ቢኖረውም በሀገር ቤት ግን ለጎሳ ግጭት መንስኤ ሆኗል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ከስልጣን ባነሷቸው አስተዳዳሪ ምትክ ማንን እንደሚሾሙ እስካሁን ፍንጭ አልሰጡም ነው የተባለው፡፡