የሱዳን የሽግግር መንግስት መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ በካይሮ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አደረጉ፡፡
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2014 የሱዳን የሽግግር መንግስት መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ በካይሮ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አደረጉ፡፡
አልቡራሃን ወደ ካይሮ በመጓዝ ከፕሬዚዳንት አብደልፈታህ አልሲሲ ጋር ተገናኝተው በሁለቱ ሀገራት
መካከል ስላለው የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሁም በደህንነትና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት
አድርገዋል፡፡
በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ላይ የተቀመጡት ጄኔራል አልቡራሃን በሀገራቸው የተፈጠረውን
አለመረጋጋት መልክ ለማስያዝ የግብፅን ድጋፍ ጠይቀዋል ነው የተባለው፡፡
ፕሬዚዳንት አልሲሲ በበኩላቸው ግብፅና ሱዳን ታሪካዊ ወዳጅነታቸውን መሰረት በማድረግ
ችግራቸውንም በጋራ ለመካፈል ዝግጁዎች ናቸው ብለዋል፡፡
መሪዎቹ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን የአባይ ውኃ ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦቸ ምን ያህል የብሔራዊ
ደህንነት ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል፡፡
በመሆኑም አሁንም ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት አጠቃቀም በተመለከተ አስቀድማ አስገዳጁን ህግ
መፈረም አለባት በሚለው ሀሳብ ትኩረት ሰጥተው ተወያይተዋል ሲል ኢጂፕት ቱዴይ ዘግቧል፡፡
ሚድል ኢስት ሞኒተር ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ባለፈው ዓመት
ከአምስት የምስራቅ አፈሪካ ሀገራት ጋር ወታደራዊ ስምምነቶችን የፈረመችው ግብፅ በርካታ የአፍሪካ
ሀገራትን ከጎኗ የማሰለፍ ጥረቷን ቀጥላለች ብሏል፡፡
የጄኔራል አልቡራን ጉብኝትና ውይይትም ይሄንኑ የግብፅ እቅድ የሚደግፍ በመሆኑ በጋራ እንስራ
የሚለውን ሀሳብ ካይሮ ከራሷ ፍልጎት አጣጥማ ታስኬደዋለች ነው የተባለው፡፡
በሱዳን መፈንቅለ መንግስት መካሄዱን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ጫና እየበዛባት መሆኑን
መነሻ በማድረግም በድጋፍ ሳቢያ በግድቡ ዙሪያ የተጨበጠ አቋም የሌላትን ካርቱምን ወደ መስመር
ለማስገባትም ጥሩ ጊዜ ሊሆንላት ይችላል የሚል ግምትም አለ፡፡