የቀድሞው የኢንሳ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ተወልደ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሰረተባቸው፡፡
ከሳምንታት በፊት በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ተወልደ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሰረተባቸው።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ክፍል ከአቶ ቢኒያም በተጨማሪ፥ ባለቤታቸው ወይዘሮ ጽጌ ተክሉ፣ በኢንሳ የስልጠናና ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር አቶ ሰላምይሁን አደፍርስና በኢንሳ የብሄራዊ ሳይበር መከላከል ሀይል አገልግሎት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ይርጋለም አብርሀ ላይም ክስ መስርቷል።
በአንደኛ ክስ ላይ እንደተጠቀሰው 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ከአሰራር ውጭ በሆነ መንገድ የግል ጥቅምን ለማካበት በማሰብ፥ ሀምሌ 9 ቀን 2008 ዓ.ም የሳይበር ታለንት ማኔጅመንት ፕሮግራም ሚስጥራዊ አገልግሎት ግዥ ለመፈጸም አቮርኒጋ ቴክኖሎጅ ሊሚትድ ከተባለ የእስራኤል ድርጅት ጋር ከ72 ሚሊየን ብር በላይ የስልጠና አገልግሎት ግዥ ውል ፈጽመዋል።
በውሉ መሰረት ሶስት አይነት ክፍያ አፈጻጸም ስላለው 32 ነጥብ 4 ሚሊየን ብሩን ስልጠናው ሲጠናቀቅ በሰርተፍኬቱ መሰረት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መውጣት ቢኖርበትም፥ ምንም አይነት ስልጠና ሳይሰጥና ከድርጅቱ ጋር በመመሳጠር ገንዘቡ እንዲከፈል መደረጉም በክሱ ተጠቅሷል።
1ኛ ተከሳሽ አቶ ቢኒያም በሌላ በኩል ከየካቲት 5 ቀን 1997 ዓ.ም አንስቶ ከ1 ሺህ 300 ብር ጀምሮ ደሞዝ እየተከፈላቸው እና ተቋማት በቀያየሩ ቁጥር ክፍያቸውም እየጨመረ በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና በሌሎችም ተቋማት ሲሰሩ የተከፈላቸው ገንዘብ 1 ነጥብ 64 ሚሊየን ብር መሆኑም በክሱ ተመላክቷል።
ነገር ግን ገንዘቡን በባለቤታቸው ስም በማድረግ 1 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታን የሚሸፍኑ የተለያዩ ቦታዎችና ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችና መሰል ሀብቶችን፥ በአጠቃላይ በህጋዊ አግባብ ካገኙት ገንዘብ በተጨማሪ ከ9 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመትና ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ማፍራትም በክሱ ቀርቧል።
በሶስተኛ ክስ አንደኛ ተከሳሽ አቶ ቢኒያምና ባለቤታቸው ምንጩ ያልታወቀ ሀብት በማፍራትና ወንጀልን ለመሸሸግ በባለቤታቸው ስም በማድረግ፥ በፈጸሙት በሙስና ወንጀል የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
በአራተኛና አምስተኛ ክስም አንደኛ ተከሳሽ ከህግ አግባብ ውጭ በቤታቸውና በእጃቸው ከ10 ሺህ ዶላር በላይና ማካሮቭ ሽጉጥ ከዘጠኝ ጥይት ጋር ተገኝቶባቸዋል ተብሏል።
በሌላ ክስም 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የሚሆነው ህጋዊ ገቢያቸው ተብሎ ቢለይም በወይዘሪት ነጻነት ዘውዱና በራሳቸው ስም ከ7 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ያፈሩ በመሆኑ ምንጩ ባልታወቀ ንብረት ማፍራት ወንጀልም ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግም ከክሱ በተጨማሪ ያለ አግባብ ተመዝብረዋል የተባሉትና በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ቦታዎች፣ ድርጅቶች፣ ጥሬ ገንዘብና በክሱ የተጠቀሱት የወንጀል ንብረቶች ተወርሰው ለመንግስት ገቢ እንዲሆኑም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ክሱን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ተረኛ የወንጀል ችሎት በቀረበው ክስ ላይ ተከሳሾች ምላሽና ክርክር እንዲያደርጉ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ኤፍ ቢ ሲ