የቤተክርስቲያኗን የአደባባይ በዓላት በአለማዊ ክንዋኔዎች እንዳይበረዙ መጠበቅ ያስፈልጋል ተባለ::
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 4 ፣ 2013 የቤተክርስቲያኗን የአደባባይ በዓላት በአለማዊ ክንዋኔዎች እንዳይበረዙ መጠበቅ ያስፈልጋል ተባለ::የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ፅህፈት ቤት የሰበካ ጉባኤ የአደባባይ በዓላት ስኬቶችና ተግዳሮቶች በሚል ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የቤተክርስቲያኗን የአደባባይ በዓላት የበዓላቱን አከባበር ዝግጅት የሚያስተባብር ቋሚ አደረጃጀት ሊኖር ይገባል ብሏል፡፡
በጉዳዩ ላይ መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት መምህር ማለዳ ዘሪሁን ቤተክርስቲያኗ የምታከብራቸው በዓላት ሃይማኖታዊ አስተምሮት ስርዓትን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ቤተክርስቲያኗ የአደባባይ በዓላት ከስርዓቱ ያፈነገጡ ዓለማዊ ተግባራት እየታዩ መምጣታቸውን በአላቱ ተግዳሮት እንዲያጋጥማቸው እና ይዘታቸው እንዲበረዙ እያረገ መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡
እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አገረ ስብከት ድረስ ኮሚቴ በማዋቅር ምዕመኑ ከቤተክስቲያኗ ጋር ማስተሳሰር እንደሚጠበቅበት በእለቱ ተገልጿል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ በዓላቱ ሀይማኖታዊ ይዘታቸው ሳይሸረሸር
እንዲከበር ምዕመኑን የማስተማር ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
የመድረኩም ተሳታፊዎች የአደባባይ በዓላት በሚከበሩበት ስፍራዎች የሚደረጉ አለማዊ ተግባራት ስርዐቱን የሚያበላሽ በመሆናቸው ሊታረሙ ይገባል ሲሉ አስታየታቸውን መስጠታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡በመጨረሻም የአደባባይ በዓላት የሚከበርባቸው ቦታዎች ተገቢውን ክብርና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡