የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን በመቀለ ከተማ መክፈቱን አስታወቀ።
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2012የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን በመቀለ ከተማ መክፈቱን አስታወቀ።
የፓርቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወሉ አብዲ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ ብልጽግና ፓርቲ አገራዊ ፓርቲ በመሆኑ በሁሉም ክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹን ከፍቶ እንደሚንቀሳቀስ ቃል በገባው መሰረት የትግራይ ክልል ቅርንጫፉን በመቀለ ከተማ ከፍቷል።
የትግራይ ክልል የለውጡ አንድ አካል በመሆኑ የትግራይን ህዝብ በለውጡ ተጠቃሚ በማድረግና የብልጽግናው ጉዞ አጋር እንዲሆን ፓርቲው በቅርቡ ጽህፈት ቤቱን ይከፍታል ብሎ ቃል በገባው መሰረት ይሄንኑ ቃሉን መፈጸሙን ነው አቶ አወሉ የገለፁት።
የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሆነው የተመደቡት አቶ ነብዩ ስሑል ሚካኤል በዚሁ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ቀደም ባሉት ጉዚያት ለትግራይ ህዝብ ተጠቃሚነት ሲታገሉ ቆይተዋል፤ አሁን ደግሞ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የመጣውን ብልጽግና ፓርቲ በመቀላቀል የትግራይ ህዝብን ወደ ብልጽግና ለማድረስ እሰራለሁ ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ለውጥ የወለደው አገራዊ ፓርቲ ነው ያሉት አቶ ነብዩ፤ አገራዊ ለውጡን አገራዊ ከማድረግ አንጻር ፓርቲው በትግራይ ክልል ጽህፈት ቤት መክፈቱ ተገቢና ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ አቶ ነብዩ ገለጻ፤ ለውጡ መደመርን ይዞ የመጣና ይህ የመደመር እሳቤ ደግሞ ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ መስዋዕትነት ለከፈለው የትግራይ ህዝብ ብልጽግና ትልቅ እድል ነው ብለዋል።
ብልጽግና በሁሉም ወረዳዎችና ዞኖች ቢሮዎችን በቅርቡ እንደሚከፍትና አደረጃጃቱን እነደሚያሰፋ የገለጹት አቶ ነብዩ፤ ተመሳሳይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትም በአዲስ አበባ ይኖረዋል ብለዋል።