loading
የትምህርትን የጥራት ችግር ለመፍታት በልዩ ትኩረት ይሰራል-ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 በትምህርት ስርአቱ ላይ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር ለመፍታት የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ። ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አዲስ ከተመደቡት የከፍተኛ ትምህርት የቦርድ አመራሮች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዘርፉ የአምስት አመት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ማረጋገጥ በመሆኑ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።


ለዚህ እቅድ ስኬትም አጠቃላይ የማህበረሰቡና የትምህርት ተቋማት ድርሻ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው አዲስ የተመደቡት  የከፍተኛ ትምህርት የቦርድ አመራሮችም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የቦርድ አመራሮቹ በበኩላቸው በሚኒስቴሩ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ውጤታማ እንዲሆን ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።


በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሙስናና ብልሹ አሰራር እየተበራከተ መምጣቱን ጠቅሰው ችግሩን ለመፍታት የጋራ ጥረት ማድረግ ይገባል ብለዋል። የትምህርት ተቋማት የእውቀት ማእከላት እንጂ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያዎች መሆን ስለሌለባቸው ለዚህም በልዩ ትኩረት መስራትን ይጠይቃል ነው ያሉት። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ የሆኑ ብቁ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ምሁራን መፍለቂያዎች ሊሆኑ ይገባልም ብለዋል።


የከፍተኛ ትምህርት የቦርድ አመራሮች ጋር የተደረገው የውይይት መድረክም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን የሪፎርም ስራ ለማሳካት ያግዛል ተብሏል፡፡
ለትምህርት ጥራት ስኬት ተማሪዎች ከታች ጀምሮ ተገቢና በቂ የትምህርት እውቅት እያገኙ እንዲያድጉ ማድረግ ይገባል ብለዋል ተወያዮቹ።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *