የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው
የህዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና ስቴት ካውንስልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ዋንግ ይ ከታህሳስ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ።
ዋንግ ይ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እንዲሁም ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ውይይት ያደርጋሉ።
የአሁኑ የሚኒስትሩ ጉብኝት ዓላማ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የጠበቀና ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ፓርትነርሽፕ ትብብር ለማስቀጠል እና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ያለመ ነው።
ዋንግ ይ የፈረንጆቹ 2019 ዓመት በገባ በመጀመሪያው ወር የመጀመሪያው ሳምንት የመጀመሪያዎቹ ቀናት በኢትየጵያ የሚያደርጉት ይፋዊ ጉብኝታቸው ሁለቱ አገሮች ያላቸውን ታሪካዊ እና የቆየ ወዳጅነት ጥልቅነት የሚያሳይ ነው።
እንደ ውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ገለፃ ሁለቱ አገሮች ከግንቦት ወር 2009 ዓም ጀምሮ ግንኙነታቸውን ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ፓርትነርሽፕ ትብብር ደረጃ ማሳደጋቸው ይታወቃል። ትብብሩም በሁለትዮሽ፣ በባለብዙ ወገን፣ በህዝብ ለህዝብ፣ በንግዱ ማህበረሰብ እናበሌሎችም የተደገፈ እና ሁሉን አቀፍ ነው።