የአልቃይዳ የሰሜን አፍሪካ መሪ አብደልማሌክ ድሩክደል በፈረንሳይ ጦር ተገደሉ፡፡
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2012 የአልቃይዳ የሰሜን አፍሪካ መሪ አብደልማሌክ ድሩክደል በፈረንሳይ ጦር ተገደሉ፡፡ የፈረንሳይ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አብደልማሌክ ድሩክደል በሰሜናዊ ማሊ ግዛት በፈረንሳይ ወታደሮች መገደሉን አስታውቋል፡፡ እንደ አልጄዚራ ዘገባ የሰሜን አፍሪካ የአለቃይዳ አዛዥ በማሊ ለሰባት ዓመታት በፈረንሳይ ወታደሮች ሲታደን መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በሽብረተኛ ቡድን መሪው መገደል ዙሪያ ከአልቃይዳ በኩል ምንም የተባለ ነገር የለም፡፡ ከስድስት ወራት በፊት በፈረንሳዩ ፕሬዜዳንት ኢማኑኤል ማክሮንና በቡድን 5 የሳህል አባል ሀገራት መካከል ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የሽብርተኛ ቡድኖችንና አይ ኤስ አይ ኤስን ለመዋጋት ወታደራዊ ሃይላቸውን ለማጣመር ከስምምነት ደርሰው ነበር፡፡ የማሊ ቅኝ ገዢ የነበረችው ፈረንሳይ በቀጠናው 600 ተጨማሪ ወታደሮችን ያሰማራች ሲሆን ይህም በዚያ ያላትን የወታደር ቁጥር ወደ 5 ሺህ አንድ መቶ አሳድጎታል፡፡