የአማራ ብልጽግና በአማራ ክልል የተካሄዱትን ሰልፎች ለራሱ አላማ በሚያመች መልኩ ሲያስታባርና ሲመራ የዋለው አካል ማን አንደሆነ በግልፅ የታየበት ነው አለ፡፡
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2013የአማራ ብልጽግና በአማራ ክልል የተካሄዱትን ሰልፎች ለራሱ አላማ በሚያመች መልኩ ሲያስታባርና ሲመራ የዋለው አካል ማን አንደሆነ በግልፅ የታየበት ነው አለ፡፡ፓረቲዉ ባወጣዉ መግለጫ ያጋጠመንን ፈተና የምንሻገረው እውነተኛ ሕዝባዊነታችን ጠብቀን በመዝለቅ ነው ብሏል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ መታረም ያለባቸው ውስጣዊ ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው የችግሮቻችን ሁሉ የመጀመያው የትህነግ የክህደት ቡድን ሀገረ-መንግሥቱን የማፈረስ የጥፋት ሚና ነዉ ብሏል፡፡ቀጥለው ኦነግ ሸኔ፣ የጉምዝ ታጣቂ ኃይልና በተከበረው የቅማንት ሕዝብ ስም የሚነግደው ቅጥረኛው ታጣቂ የሽፍታ ቡድን የችግሮቻችን ምንጭና የጥፋት ዘር የሚዘሩ ዋና የአገርና የህዝብ ጠላቶች መሆናቸዉን ፓርቲዉ ገልጿል፡፡
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ እስከመጨረሻው የሚታገለው በዘር ጥላቻ የመታወር የመርዘኛ አስተሳሰብ ድርጊትና ውጤት ነው ብሎ ያምናል ያለዉ ፓርቲዉ፤ በዚህ አጋጣሚ በማንነታቸው በግፍ ለተጨፈጨፉና ለሞቱ ቤተሰቦች፣ የተፈጠረውን ችግር ለማስቆም መስዕዋትነት ለከፈሉ የፌደራልና የክልላችን የፀጥታ ኃይሎች ከልብ የመነጨ መፅናናትን እንመኛለን ብሏል፡፡በክልሉ የተካሄደዉን ሰልፍ ተገቢ ነዉ ያለዉ መግለጫዉ፤ በሰልፉ የተነሱ ሀሳቦች ትክክል ናቸዉ ብሎ እንደሚያምንም ገልጿል፡፡ማመን ብቻ ሳይሆን የአማራ ህዝብ ሞትና መፈናቀል በዘላቂነት እንዲቆም ይታገላል፤ በተጨባጭም የፖለቲካና የጸጥታ ስራዎችን ሌትና ቀን እየሰራ ይገኛል ብሏል፡፡
ይሁን እንጂ የተካሄዱ ሰልፎች ምንም እንኳ በሰላም ተጠናቀቁ ይባል እንጅ በአንዳንድ ከተሞች ከተጠሩበት ሕዝባዊ ዓላማ ውጭ ሆነው አግኝተናቸዋል ያለዉ ፓርቲዉ ፤ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ምርጫው በሰላማዊና ዴሞከራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ስራ ላይ ባለበት በተቃራኒው ዓላማ ተይዞ የተካሄደ በመሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡የሰልፎቹ አላማ በጽንፈኛ ኃይሎች ተጠልፎ የእነሱ ተልዕኮና የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ለማድረግ ሙከራ መደረጉን በመግለጫዉ ተጠቅሷል፡፡
ምንም እንኳ እነዚህ በሰልፉ የተሳተፉና ከሰልፉ አላማ ውጭ ሲንቀሳቀሱ የተስተዋሉ አካላት/ቡድኖች የአማራ ክልል ህዝብን የሚወክሉ ባይሆኑም ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ፣ ፊት የሚያዟዙሩ፣ ጥላቻና መጠራጠርን የሚያሰፉ አሳፋሪ ኩነቶችን ሲያከናውኑ ተስተውለዋል፡፡በዚህ ሰልፍ የታየው አፍራሽ እንቅስቃሴ ፓርቲያችን ብልጽግናን በማውገዝ ላይ የተመሰረተ የአማራን ክልል የሁከትና የብጥብጥ ማእከል በማድረግ ቀጥተኛ ተጠቂና ህዝባችን ለአደጋ ተጋላጭ እንዲሆን የሚያደርግ ነው በመሀኑ ፤ይህ ድርጊት የአማራ ህዝብ ያለበትን የፀጥታና የፖለቲካ ሁኔታ ያላገናዘበና ይልቁንም ለከፋ ሁኔታ የሚዳርግ የተሳሳተ መንገድ ሆኖ እንደሚታይ ፓርቲዉ ገልጿል፡፡
የሰልፉ ታዳሚ ከጥቂት ግለሰቦች እኩይ ተግባራት በተጨማሪ ፤ከአብን በስተቀር የብልጽግና ፓርቲ እና የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክትና ባነሮች ከተሰቀሉበት ቢልቦርድ ወርደው እንዲቃጠሉና እንዲቀደዱ ተደርጓል፡፡በአንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ አሰፈፃሚዎች ተረጋግተው ስራቸውን እንዳይሰሩ ወከባ ሲፈጥሩ የዋሉም አሉ፤ይህም የህዝቡን እውነተኛና ፍትሀዊ ጥያቄ ጠልፎ ለራሱ ስግብግበ አላማ በሚያመች መልኩ ስልፉን ሲያስታባርና ሲመራ የዋለው አካል ማን አንደሆነ በግልፅ የታየበት ነው ብሏል፡፡