የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ለሰብአዊ ድጋፍ ከ53 ሚሊየን ዩሮ በላይ ድጋፍ አደረገ፡፡
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2013 የአውሮፓ ህብረት በትግራይና ሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች የሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች 53 ነጥብ 7 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አድርጓል፡፡ድጋፉ በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ጨምሮ በግጭትና በአየር ንብረት ለተጎዱ ወገኖች የሚውል እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
የህብረቱ የቀውስ አመራር ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺቺ ድጋፉ ትግራይ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ ማድረስ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በተለያየ መልኩ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳትና በሚገኙበት አካባቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ ይውላልም ተብሏል፡፡
ኮሚሽነሩ በነገው ዕለት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር እንደሚወያዩ ከህብረቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡