loading
የአየር ላንድ መንግስት ቅርሶችን በአረንጓዴ ብርሃን ማስዋብ በሚል በላሊበላ የአረንጓዴ ብርሃን ዝግጅት አካሄደ

የአየር ላንድ መንግስት ቅርሶችን በአረንጓዴ ብርሃን ማስዋብ በሚል በላሊበላ የአረንጓዴ ብርሃን ዝግጅት አካሄደ፡፡

ዝግጅቱ ቅርሶችን በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ያለመ ነው ተብሏል። ያም ሆኖ የአንድ ምሽቱ ተግባር ከዚህ ቀደም ከተያዘውና ላሊበላን በዘላቂነት ለማስተዋወቅ ያለመ ነው ከተባለው ፕሮጀክት ጋር አልገናኝ ማለቱ ለብዙዎች ጥያቄ ፈጥሯል ። የአርትስ ሪፖርተር ከስፍራው ያጠናቀረችው ዘገባ እንደሚያስረዳው።

በያዝነው ወር አየርላንድ እና ኢትዮጵያም የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን 25ኛ አመት የብር እዩቤልዩ በአል እያከበሩ ነው፡፡ የዚህ ክብረበዓል አንዱ መርሃግብር የሆነውንና የላሊበላን አብያተክርስቲያናት በአረንጓዴ መብራት የማስዋብ ፕሮጀክት ተጠናቆ ስራው በይፋ መጀመሩን ለማብሰር ባሳለፍነው ቅዳሜ ከላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት መካከል አንዱ በሆነው በቤተ ጊዮርጊስ ህንፃ ቤተክርስቲያን ላይ አረንጓዴ መብራቶች ተገጥመው የአንድ ምሽት ፕሮግራም ተካሂዷል። ይህንን ፕሮግራምም በስፍራው  ተገኝተን ተመልክተናል፡፡

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት በባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ልማት ዘርፍ አማካሪው አቶ ገብርኤል አስፋው የአንድ ምሽት አረንጓዴ መብራቱ ዝግጅቱ ቅርሶችን በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን ነው ለአርትስ የሚናገሩት ፡፡

ከአየር ላንድ ኢምባሲ ተወክለው በዝግጅቱ ወቅት የነበሩት ሚስተር ፓትሪክ ማናውስ በበኩላቸው የዚህ የግሪኒንግ ወይም ቅርሶችን በአረንጓዴ ብረሃን የማስዋብ ዝግጅት የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር እና ቅርሶቹን በተለያዩ መንገዶች ለአለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ጥቅም አለው ብለዋል፡፡

ዝግጅቱ በዚህ መልክ ይገለጽ እንጂ ባለፈው ጥር ወር የአየር ላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ይተገበራል ተብሎ ከተገባው ቃል ጋር የተገናኘ አይመስልም።

በጥር ወር የአየርላንድ መንግስት ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እ.ኢ.አ ከ2019-2021 ድረስ የሚቆይ በባህላዊ ቅርሶች እና በገጠር ቱሪዝም ላይ በጋራ ለመስራት ያለመ ፕሮጀክት መነደፉ ይፋ ተደርጎ ነበር።

ይህንን ተከትሎም  በአየርላንድ መንግሰት ድጋፍ  ላል ይበላን ቀንና ማታ መጎብኘት የሚያስችል የአረንጓዴ ብርሃን ቴክኖሎጂ ሊተገበር እንደሆነ ተናግረው አርትስ ቴሌቪዠንም በስፍራው ተገኝቶ ይህንኑ ዘግቦ ነበር።

የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሳው በጊዜው እንደተናገሩት  ከአየር ላንድ መንግስት ጋር የቅዱስ ላል ይበላ አብያተ ክርስትያናትን በቀንና ማታ መጎብኘት የሚያስችል የአረንጓዴ ብርሃን ቴክኖሎጂ ይተገበራል ። ይህም ከፍተኛ የቱሪዝም ፍሰትን የሚጨምር እና ለቅርሱም ልዮ መስህብን የሚያጎናፅፍ ነው ፡፡

በአየርላንድ በኩልም ይሁን በኢትዮጵያ አቻ ሃላፊዎች  በጊዜው የተነገረው ይህ የአረንጓዴ ብርሃን ቴክኖሎጂም የቅዱስ ላል ይበላ አብያተ ክርስትያናትን በቀንና ማታ መጎብኘት የሚያስችል እንደሞሆን ነበር፡፡

አሁን በቤተ ጊዮርጊስ ላይ የተተገበረው የአረንጓዴ መብራት መርሀግብር ግን ከዚህ ሃሳብ ጋር የሚሄድ አልሆነም። በተቃራኒው ጊዜያዊው እና ለአንድ ምሽት የቆየው አረንጓዴ መብራት  በካሜራ ተቀርፆ አብቅቷል። ይህም በዓለምአቀፍ ደረጃ ቅርሶቹን ለማስተዋወቅ ያግዛል ተብሏል። በምን መልኩ እና እንዴት ይህ ሰፊ ሃሳብ በአነድ ምሽት መብራት ተግባራዊ ይሆናል የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ማብራሪያ ግን አልተገኘም።

የ25ኛ አመት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የብር እዮቤሊዮ እያከበሩ ያሉት ኢትዮጵያ እና አየር ላንድ ይህን የአረንጓዴ ብረሀን ማስዋቢያ ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከሪያ ይውላል ባዮች ናቸው።  የኢምባሲው ተወካይ ሚስተር ፓትሪክም የሚያጠናክሩት ይህንኑ ሃሳብ ነው። ይህ የላይልበላ አብያተክርስቲያናትን በአረንጓዴ ብረሃን ማስዋብ የ25ኛ አመት ወዳጅነት ክብረበአል አካል ነው ብለውናል።

ቅርሶችን በማስተዋወቅ ረገድ የባህል እና ቱሪዝም ዘርፉ ላይ ኢትዮጵያ ካሏት ቅርሶች አንፃር ብዙ እንዳልተሰራ ይነገራል፡፡  ይህ የአረንጓዴ ብረሃን ቴክኖሎጂ አንደሚባለው ቅርሶቹን ለማስተዋወቅ ጠቀሜታ ቢኖረውም  ቅሉ የላይልበላ አብያተክርስቲያናት ግን ከጊዜአዊ ማስዋቢያ ይልቅ በዘላቂነት አፋጣኝ ጥገና ሊደረግላቸው የሚገባቸው ጊዜ ላይ ናቸው።

ይህንንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥናቱ አረጋግጧል፡፡

አርትስ ቴሌቪዠን እንደታዘበው ላሊበላ ላይ የጎብኚዎችን ፍሰት ለመጨመር እና የተሻለ ገቢ ለማግኘት ቅርሶቹ አሁን ካሉበት ደረጃ በባሰ ሳይጎዱ የሚተርፉበት መንገድ ሊፈለግ ይገባል።  ይህንን ውድ ቅርስ ከጊዜአዊ ማስዋቢያነት በተሻለ ተገቢውን እድሳት በማድረግ ከመፍረስ መታደግ የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ መሆን ይገባዋል።

 

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *