loading
የአፍሪካ ህጻናት ቀን የኢኮኖሚ ጫና ለገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግ እየተከበረ ነው::

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2012 የአፍሪካ ህጻናት ቀን የኢኮኖሚ ጫና ለገጠማቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግ እየተከበረ ነው:: የአፍሪካ ህጻናት ቀን በኮቪድ-19 ምክንያት የኢኮኖሚ ጫና ለገጠማቸው ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግና ግንዛቤ በመስጠት እየተከበረ መሆኑን የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ :: ሚኒስቴሩ ለአርትስ በላከዉ መግለጫ እንዳስታወቀዉ የአፍሪካ ህጻናት ቀንን ከሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በዓሉን እያከበረ ሲሆን ”ህጻናትን ከወረርሽኝና ከጥቃት በመታደግ አረንጓዴ ልማትን ባህል ያደረገ ትውልድ እንፍጠር” በሚል መሪ ቃል ነው:: በዓሉን ህጻናት፣ ባለድርሻና አጋር አካላት በመሳተፍ በተለያዩ የትምህርት ሰጪ መርሃግብሮች እያከበሩት ይገኛሉ ::

በኤስ.ኦ.ኤስ የህጻናት መንደር ሲከበር የተገኙት የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ወይዘሮ ፌልሰን አብዱላሂ ቀኑ በህጻናት ላይ የሚፈጸመውን ግፍ በማውገዝ የህጻናትን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል:: የዘንድሮ የአፍሪካ ህጻናት ቀንን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመርዳት ጭምር እየተከበረ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል:: ለእዚህም በአዲስ አበባና በክልል ላሉ የሴቶችና ህጻናት መንደር ማዕከላት የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ መደረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል:: “ወላጆችና ማህበረሰቡ ለህጻናት መልካም አርአያ በመሆን በቀጣይ ህጻናት አካባቢያቸውን የሚወዱና የሚንከባከቡ እንዲሆኑ ኃላፊነቱን መወጣት አለባቸው” ብለዋል :: በህጻናት ጉዳይ የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ አካላትም ህጻናት ሊፈጸሙባቸው ከሚችሉ የተለያዩ ጥቃቶችና ሊገጥሟቸው ከሚችሉ ችግሮች ሊታደጓቸው እንደሚገባ አመልክተዋል :: የአፍሪካ ህጻናት ቀን እኤአ በ1976 በደቡብ አፍሪካ ስዌቶ ከተማ በግፍ የተጨፈጨፉ ንጹሃን ታዳጊ ህጻናትን ለማስታወስ በየዓመቱ ሰኔ 9 የሚከበር መሆኑ ይታወቃል::

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *