የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በውጭ ሀገር ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያየ
አርትስ 29/12/2010
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከሀገር ውጭ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል።
ቦርዱ በዛሬው ዕለት የተወያየው መንግስት ባደረገው ጥሪ መሰረት ሀገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ የፖለቲካ አንቅስቃሴ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሳሚያ ዘካሪያ በዚሁ ወቅት፥ ሀገሪቷ በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደምትገኝ እና ቦርዱም የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሚቀጥለውን ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ተዓማኒ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተጀመረና የተለያዩ ግብዓቶች እየተሰበሰቡ እንደሆኑ ሰብሳቢዋ ገልፀዋል።
የቦርዱ የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አውድሮ፥ በምርጫ ሕግ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ እና ፓርቲዎች ምዝገባ ሲያካሂዱ ማሟላት የሚገባቸው መስፈርቶች እና የፓርቲዎች መብትና እና ግዴታ ላይ ፅሑፍ አቅርበዋል።
በቀረበው ፅሑፍ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው በቦርዱ ሰብሳቢ እና በጽህፈት ቤቱ አመራሮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ኤፍ.ቢ.ሲ