loading
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተስተካካይ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ

በ21ኛው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሀግብር ቅዳሜ እና ዕሁድ ሀዋሳ ከተማ ላይ መካሄድ የነበረባቸው፤ ነገር ግን በደጋፊዎች ግጭት ምክንያት ያልተካሄዱ ሁለት ግጥሚያዎች ዛሬ ይከናወናሉ፡፡

ቅዳሜ መደረግ የነበረበት እና ከጨዋታው ጅማሮ በፊት በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ለዛሬ የተገፋው የደቡብ ፖሊስ እና ወላይታ ድቻ ፍልሚያ ቀን 11፡00 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በዝግ ስታዲየም ይከናወናል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የደረጃ ሰንጠራዥ 12ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን በመሀላቸው ያለው የነጥብ ልዩነት አምስት በመሆኑ፤ በተጨማሪም የወራጅ ቀጠና ስጋት ስላለባቸው ጥሩ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የፖሊሱ ቡድን ድል የሚቀናው ከሆነ ነጥቡን ወደ 21 በማድረስ ከመውረድ ስጋት ለመገላገል የሚያደርገውን ጉዞ የሚያስቀጥል ይሆናል፡፡ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ድቻ ደግሞ የሚያሸንፍ ከሆነ ነጥቡን ወደ 26 ያሳድጋል፡፡

ጨዋታው በኢንተርናሽናል አርቢትር ለሚ ንጉሴ ይመራል ተብሏል።

ሌላኛው ግጥሚያ በሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ መካከል 9፡00 ላይ በአሰላ ስታዲየም ይደረጋል፡፡ ይህ ጨዋታ ከደቡብ ፖሊስ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ አስቀድሞ የተፈጠረውን የደጋፊዎች ጥል ተከትሎ በተፈጠረው የደህንነት ውጥረት ምክንያት የክልሉ ፖሊስ የጥበቃ ሃላፊነት አልወስድም በማለቱ ከሀዋሳ ወደ አሰላ ተላልፏል ፡፡

ጊዮርጊስ የሚረታ ከሆነ ደረጃውን ወደ አራተኛ የሚያሻሽል ይሆናል፤ በተቃራኒው ሀዋሳ ከጨዋታው ሶስት ነጥብ የሚያገኝ ከሆነ በ32 ነጥብ የኢትጵያ ቡናን የስድስተኛ ደረጃ ይረከባል፡፡  

ኢንተርናሽናል አርቢትር ሊዲያ ታፈሰ ይህንን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት እንድትመራ ኃላፊነት ተሰጥቷታል።

መቐለ 70 እንደርታ ሊጉን በ45 ነጥቦች ይመራል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *