የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሀንት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለዉን ለዉጥ እደግፋለሁ አሉ፡፡
የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሀንት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለዉን ለዉጥ እደግፋለሁ አሉ፡፡
ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ከጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ ጋር በጠቅላይ ሚኒስተሩር ጽ/ቤት በነበራቸዉ ዉይይት ነዉ፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ለረጅም ግዜ ለቆየው የእንግሊዝ መንግስት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ጀርሚ ሀንት በበኩላቸው የእንግሊዝና ኢትዮጵያ መንግስታት መካከል ያለው ግንኙነት እንደሚቀጥል አስታውቀው በተለይም አሁን እየተካሄደ ላለው ለውጥ ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል።
የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ከእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሃንት ጋር በጽ/ቤታቸው ተወያይተዋል።
ሁለቱ አቻ ሚኒስትሮች በሁለትዮሽ እና በክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት አድርገው መክረዋል።
አቶ ገዱ በዉይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በለውጥና በዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ የምትገኝ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ እንግሊዝ እያደረገች ላለው ሁሉን አቀፍ ድጋፍም አመስግነዋል።
አቶ ገዱ የአካባቢው ሰላም ከኢትዮጵያ ሰላም ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ በስፋት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች ብለዋል። ከኤርትራ ጋር ስለተደረሰው የሰላም ስምምነትም ለጀርሚን ገለጻ አድርገዋል።
በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍንም ኢትዮጵያ ተስፋ ሳትቆርጥ ትሰራለች ብለዋል፡፡
የእንግሊዝ ባለሀብቶች በአገራችን እያደረጉ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ያደነቁት አቶ ገዱ፤ እንግሊዝ በአገራችን በንግድ እና በኢንቨስትመንት ያላትን ጉልህ ድርሻ አጠናክራ እንደምትቀጥል ሙሉ እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሃንት በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየወሰደች ያለውን ቆራጥ የሪፎርም ሂደት አድንቀዋል፤ ለዚህም እንግሊዝ ሙሉ ድጋፏን ትሰጣለች ብለዋል ።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን እንዲሆን እንግሊዝ የዲሞክራሲ ተቋማትን አቅም በማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላም እንዲስፍን እያደረገች ያለውን ሰፊ ስራም እንግሊዝ ታደንቃለች ብለዋል። እንግሊዝ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍንም ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃላቀባይ ጽ/ቤት እንዳገኘነዉ መረጃ ከአፍሪካ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ በለንደን ኤምባሲዋን በመክፈት የመጀመሪዋ አገር ናት ።