loading
የእንግሊዝ ፕሪምየር የመዝጊያ ጨዋታዎች በመጪው ዕሁድ ይደረጋሉ፡፡

የ2018/2019 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመት ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት መርሀግብር ብቻ ይቀረዋል፡፡ ይህ የሊግ ውድድር አሸናፊውን ቡድን ሳይለይ ልብ እንዳንጠለጠለ ይሄው መጪው ዕሁድን ይጠብቃል፡፡

ሁሉም ጨዋታዎች በተመሳሳይ 11፡00 ሲል የሚከናወን ሲሆን የሊጉ አሸናፊ ለመሆን ማንችስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ተፋጥጠዋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች አንዳቸው ሌላኛቸውን እያስቀደሙ እና እያስከተሉ ደረጃ ሲቀያየሩ ወራትን አሳልፈው በመጨረሻም በቁርጡ ቀን ሻምፒዮን የሚሆነው ቡድን የሚለይ ይሆናል፡፡

ይሄንን ዋንጫ ለሶስት አስርት አመታት ያህል በተጣጋ ጊዜ ያላሳኩት እና ከምንም በላይ አስበልጠው የሚፈልጉት ቀያዮቹ ሊቨርፑሎች፤ የጎረቤት ያህል ቅርብ በሆነው ከተማ ውስጥ በሚገኘው ማንችስተር ሲቲ ላይ አንዳች ነገር ማለትም ሽንፈት አሊያ ነጥብ መጣልን እየተመኘ የመዝጊያ ጨዋታውን፤ በውድድር ዓመቱ ታላላቅ ቡድኖችን እየፈተነ እና ነጥብ እያስጣለ የሚገኘውን ወልቨርሃምፕተን ዋንደረርስ በአንፊልድ ሮድ ስታዲየም ያስተናግዳል፡፡

ሊቨርፑል እና ማንችስተር ሲቲ በመሀላቸው የአንድ ነጥብ ልዩነት በመኖሩ፤ ቀያዮቹ በወልቭስ ላይ ድል መቀዳጀታቸው ብቻ ሳይሆን የሲቲ ነጥብ መጣል ግድ ይላቸዋል፡፡

አሊያ ደግሞ በእንግሊዝ ከነጥብ ቀጥሎ ንፁህ የግብ መጠን የሚታይ በመሆኑ እና ሲቲ ከሊቨርፑል በአራት ጎሎች ብቻ የሚልቅ በመሆኑ የመርሲ ሳይዱ ቡድን አቻ ወጥቶ የፔፕ ጓርዲዮላ ቡድን በብራይተን ከአራት ጎል በዘለለ የሚሸነፍ ከሆነ ዋንጫው የቀያዮቹ ይሆናል፡፡

የመርሲ ሳይዱ ቡድን ባለፉት ዓመታት ይሄንን ዋንጫ ወደ ካዝናው ለመቀላቀል እያለመ ሳይሳካለት የቀረ ሲሆን የዘንድሮውን የመጨረሻ ጨዋታ በሜዳው አንፊልድ ሮድ ስታዲየም የሚያደርግ በመሆኑ ከማክሰኞው የቻምፒዮንስ ሊጉ የመልስ ጨዋታ ታዕምር መልስ ዋንጫውን ከፍ በማድረግ በድጋሜ ከደጋፊው ጋር you will never walk alone የሚለውን ዝማሬ ለማዜም ጨዋታው የሚደረግበትን ሰዓት በጉጉት ይጠብቃል፡፡

ይህ ዋንጫ የሚሳካ ከሆነ ከሶስት ሳምንታት በኋላ ማድሪድ ላይ በሚደረገው የቻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ጨዋታ ክለቡ ከቶተንሃም ጋር ለሚያደርገው ፍልሚያ ትልቅ ማነሳሻ ይሆነዋል፡፡

የፔፕ ጓርዲዮላው ማንችስተር ሲቲ ወደ አሜክስ ስታዲየም አምርቶ ከብራይተን ጋር ጨዋታውን የሚፈፅም ሲሆን ማሸነፍ አሊያ የሊቨርፑል ነጥብ መጣል በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ እንዲያሳካ ያደርገዋል፡፡

በደቡብ እንግሊዝ ጠረፍ ላይ የሚገኘው እና በክሪስ ሁተን የሚሰለጥነው ቡድን ብራይተን እና አልቢዮን በሊጉ እንደሚቆይ ቢያረጋግጥም ለሲቲ በቀላሉ እጅ እንደማይሰጥ እየተነገረ ይገኛል፡፡

የሆላንዱን አያክስ አምስተርዳም ውጤት ቀልብሶ በመጣል በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ የአውሮፓ ቻምፐፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ የበቃው ቶተንሃም ሆትስፐር ወደ መርሲ ሳይድ በመጓዝ ጉዲሰን ፓርክ ላይ ከኢቨርተን ጋር ይጫወታል፡፡

በፕሪምየር ሊጉ በቁጥራዊ መረጃዎች የቀጣይ ዓመት የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ያላረጋገጠው የማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ቡድን በውድድር ዓመቱ የመቋጫ ጨዋታ በጣፋጮቹ ሊፈተን እንደሚችል ይጠበቃል፡፡  

የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ያረጋገጠው የማውሪዚዮ ሳሪው ቼልሲ ወደ ኪንግ ፓወር ተጉዞ ሌስተር ሲቲን ያገኛል፡፡ ሰማያዊዎቹ ትናንት ምሽት የዩሮፓ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚነታቸውን ማረጋገጣቸው ይታወሳል፡፡

የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ለማግኜት ዩሮፓ ሊግን ተስፋ ያደረገው አርሰናል የሊጉን የመጨረሻ ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ከበርንሊ ጋር ቱርፍ ሞር ላይ ይከውናል፡፡

የቀጣይ ዓመት የአውሮፓ ውድድሮች ተሳትፎው፤ በሌሎች ክለቦች ላይ ውጤት የተንጠለጠለው ማንችስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ካርዲፍ ሲቲን ይገጥማል፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች ዋትፎርድ በቪካሬጅ ሮድ ከዌስት ሃም ዩናይትድ፤ ሳውዛምፕተን በሴንት ሜሪ ከሀደርስፊልድ ታውን፤ ፉልሃም በክራቨን ኮቴጅ ከኒውካስትል ዩናይትድ፤ ክሪስታል ፓላስ በሴል ኽረስት ፓርክ ስታዲየም ከቦርንመዝ ጋር ይጫወታሉ፡፡

ሲቲ ሊጉን በ95 ነጥቦች ሲመራ፤ ሊቨርፑል በ94 ይከተለዋል፡፡

ካርዲፍ ሲቲ፣ ፉልሃም እና ሀደርስፊልድ ታውን ከሊጉ የተሰናበቱ ቡድኖች ናቸው፡፡  

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *