loading
የወጋገን ናትና የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ከሰኔ 30 ወደ ሐምሌ 7 እንደተራዘመ ተገለፀ፡፡

የወጋገን ናትና የ10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ከሰኔ 30 ወደ ሐምሌ 7 እንደተራዘመ ተገለፀ፡፡

በአትሌት ገ/እግዚያብሔር ገ/ማርያም እና በባለቤቱ በአትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ መስራችነት በየዓመቱ እየተካሄደ የሚገኘው የወጋገን ናትና 10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ በመቐለ ይካሄዳል፡፡

የዘንድሮው ሶስተኛው የወጋገን ናትና 10 ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ሰኔ 30/2011 ዓ/ም እንዲደረግ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም በቅርቡ ሀገሪቱ ላይ በተከሰተው የከፍተኛ ባለስልጣናት ህልፈት ምክንያት ወደ ሐምሌ 6/2011 ዓ/ም እንዲተላለፍ መደረጉን የውድድሩ ባለቤት ናትና ስፖርት ኤቨንትስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አዲሱ ተገኝ ለአርትስ አስታውቋል፡፡

በውድድሩ ቅዳሜ ሐምሌ 6 ለመጀመሪያ ጊዜ የወጋገን ናትና የህፃናት ሩጫ ለብቻቸው በተለያዩ የእድሜ ልዩነቶች በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ዓዲ ሐቂ ካምፓስ ስታዲየም ሲደረግ፤ ዋናው የውድድሩ የ10 ኪ.ሜ የሩጫ ውድድር በበነጋታው ዕሁድ ሐምሌ 7 መነሻና መድረሻውን በሮማናት አደባባይ በማድረግ በከተማዋ ዋና ዋና ቦታዎች በማለፍ ይከናወናል፡፡

የናትና ስፖርት ኤቨንትስ ሲመሰረት ለሀገር ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ለመስጠት እንደሆነ የተነገረ ሲሆን እንዲህ አይነት ውድድሮች ሲካሄዱ ሙያው ከሚሰጠው በተጨማሪ ማህበረሰቡ በስፖርት የታነፀ እንዲሆን ንቁ ዜጋ ለማፍራትም ያግዛል ተብሏል፡፡

ናትና ስፖርት ኤቨንትስ ጨምሮ የስፖርት ቱሪዝም እና የገፅታ ግንባታ፤ የህዝቦችን ሁለንተናዊ አንድነትና የህዝብ ንቅናቄን መፍጠር እንዲሁም ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ከማርከቱም በላይ በክልሉ ለመገንባት ለታቀዱት የአትሌቲክስ መንደሮች መሰረት ለመጣል የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን ገልጧል ፡፡

በዘንድሮው የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ የተሳታፊዎች ቁጥር ብዛት ይካፈሉበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ታዋቂ እና ወጣት አትሌቶችም የሚያደርጉት ትንቅንቅ ይጠበቃል፡፡

ለአሸናፊ አትሌቶችም የሜዳሊያ እና ከዓምናው የበለጠ የገንዘብ ሽልማት ይሰጣል ተበሏል፡፡ ከአንድ እስከ ሰባት ደረጃ ድረስ የወጡት የገንዘብ ሽልማት ሲወስዱ በሁለቱም ፆታ አንደኛ ለሚወጡት 60 ሺ ብር ሁለተኛ 30 ሺ እና ሶስተኛ 20 ሺ ብር ሽልማት እንደሚያገኙ ተነግሯል፡፡

በዚህ ዓመታዊ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር የከተማው እና የክልሉ ህብረተሰብ በተሻለ ተሳታፊ እንዲሆን የምዝገባ ጊዜው እንደተራዘመ የናትና ስፖርት ኤቨንትስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አዲሱ ተገኝ ለአርትስ ገልጧል፡፡ ምዝገባውም በክልሉ የወጋገን ባንክ ቅራንጫፎች እየተከናወነ ይገኛል፡፡

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *