loading
የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ የከፈቱት መንግሥት ለነሱ ጥቅም ባለመቆሙ ነው- የህግ መምህርና የማህበረሰብ አንቂ ሙክታር ኡስማን::

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 4፣ 2013 አንዳንድ የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ዘመቻ የከፈቱት አሁን ኢትዮጵያን እየመራ ያለው መንግሥት አሸባሪው ህወሓት ስልጣን ላይ እያለ እንደነበረው ለነሱ ጥቅም የቆመ ባለመሆኑ እንደሆነ የህግ መምህርና የማህበረሰብ አንቂው አቶ ሙክታር ኡስማን ተናገሩ። አቶ ሙክታር ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አሁን ስልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት በራሱ የሚተማመንና እና በምሥራቅ አፍሪካ ለውጥ ለማምጣት መሥራት መጀመሩ በአንዳንድ የውጭ ኃይሎች ዘንድ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል።

ኢትዮጵያ የቀረጸችውን የልማት አጀንዳ ለመላው አፍሪካውያን ምሳሌ የሚሆን ነው ያሉት አቶ ሙክታር፤ ምዕራባውያን ሀገራት የሚፈልጉት ደግሞ የእነሱን አጀንዳ የሚቀበልና የፖሊሲያቸው እንክብል የሚውጥ ሀገር ነው። ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ የማይሆን መንግሥትና ሀገር እንዲቀጥል አይፈልጉም ብለዋል። አቶ ሙክታር ኢትዮጵያ የያዘችው እስትራቴጂክ እቅድ በአስር ዓመት ውስጥ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የመሆን ራዕይ ያነገበ ነው፤ ይህም ለምዕራቡ ዓለም ሳታጎበድድ የበለጸገች ሀገር ስለሚያደርጋት የስጋት ምንጭ ሆናለች፤ እነሱ የሚፈልጉት በበሽታና በችግር እየተንከራተተ የእነሱን ዕርዳታ ጠባቂና የፖሊሲያቸው አስፈጻሚ የሆነ ደካማ ሀገርን ነው ብለዋል።

የሊቢያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙአማር ጋዳፊን የምዕራቡን ዓለም ፖሊሲ አልቀበልም በማለቱ እንዴት እንዳስወገዱት ያስታወሱት አቶ ሙክታር፤ በሶርያ፣ የመንና በሌሎችም መሰል ሀገራት ላይ ያደረጉት ይህንኑ ነው” ብለዋል፡፡ የግብፁ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲን አስወግደው አብዱልፈታህ
አልሲሲን የተኩበት መንገድም ተመሳሳይ መሆኑን ጠቁመዋል። ምዕራቡ ዓለም በአሸባሪው ህወሓት የተሰራውን ግፍ ሳያውቁት ቀርተው ሳይሆን የእነሱ ፍላጎት ሌላ ስለሆነ ነው ያሉት አቶ ሙክታር፤ እኛ እውነታውን የማሳወቅ ሥራ ብንሠራ እንኳን እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ ላይ የያዙት አቋም ላይቀይሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

Write a Reply or Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *