የዓለማችን ሀብታም እግር ኳስ ተጫዋች ማን ይመስለዎታል?
አርትስ ስፖርት 01/03/2011
ከረዥም አመታት በፊት ቅሪላ ማልፋት እንደ ከንቱ ነገር ይቆጠር የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ፈሰስ ይደረግበታል፡፡ ከክለቦች ባልተናነሰ የአንዳንድ ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋቾች ገቢ አንድ የኢትዮጵያ ክለብን አመታዊ ወጪ አንደላቆ ይሸፍናል፡፡ የትኛው እግር ኳስ ተጫዋች ነው በጣም ሀብታም? ፉትቦል ዴይሊ ባወጣው መረጃ እነዚህ 10 ተጫዋቾች ገንዘባም ናቸው ብሏል፡፡ ብዙዎች ይጠሉታል፣ በተለይ ደግሞ አፍሪካውያንና እንግሊዛውያን፤ የጥርሱን አቀማመጥ ላይ ይሳለቃሉ፣ በተናካሽነቱ ከእንስሳት ጋር ያወዳድሩታል የባርሴሎናው ኮከብ ኡራጋያዊው ሊዩስ ሱዋሬዝ በ40 ሚሊየን ዶላር ንፁህ ገቢ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ሌላኛው ላቲናዊ የአርጀንቲና ተጫዋች ሰርጅዎ ኩን አጉዌሮ በማንችስተር ሲቲ አሁንም ግብ እያስቆጠረ ነው፤ ለነዚህ ጎሎች መካሻ ደግሞ ክለቡ በዓመት 13 ሚሊየን ዶላር ይከፍለዋል፤ በ51 ሚሊየን ዶላር 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ በአንድ ወቅት በ2013 ማለት ነው፤ የዓለማችን ውድ በሆነ ገንዘብ ክብረ ወሰን ሰብሯል ዌልሳዊው ጋሪዝ ቤል፤ አሁንም ሪከርዱ በእጁ ባይገኝም አይናቅም፤ በ72 ሚሊየን ዶላር ንፁህ ገቢ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ፈረንሳያዊው ፖል ፖግባ እድሜ ለማንችስተር ዩናይትድ እያወዛገበ ሲሻው በፀጉር ስታይሉ ሲፈልግ በአቋም ዝቅና ከፍ ማለት ከሰው አፍ ወጥቶ አያውቅም፡፡ ለማንኛውም በዚህ ሁሉ ውስጥ ሁኖ ግን በ85 ሚሊየን ዶላር ገቢ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ የቼልሲው ኮከብ እና ቤልጅየማዊው ኤደን ሀዛርድ ደግሞ በስድስተና ደራጃ ላይ ሲቀመጥ 100 ሚሊየን ዶላር የገቢው መጠን ነው፡፡ ደሞዙ እና ከብራንድ የሚያገኛቸው ገቢዎች ወደ ፊት ከፍ ሊል እንደሚችል ይነገራል፡፡ የሀገሩን ሊግ ተሻግሮ ተጫዋቾች ጡረታ ወደሚወጡባት አሜሪካ አምርቶ ዲሲ ዩናይትድ በተሰኘ ክለብ ከእድሜው በላይ ምርጥ አገልግሎት እየቸረ ይገኛል ዋይኒ ሩኒ፤ በ120 ሚሊየን ዩሮ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተገኝቷል፡፡ በአራተኛ ደረጃ ላይ ደግሞ፤ የአለማችን ውዱ ተጫዋች፤ ገበያ ላይ በስሙ ብዙ እየሰራ የሚገኘው ብራዚላዊው ኔይማር ሲሆን በ140 ንፁህ ገቢ ወጣቱ ሀብታም ተጫዋች ነው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ታላቁ ዝላታን፤ ዝላታን ኢብራሂሞቪች አውሮፓን ተሻግሮም ሎስ አንጀለስ ላይ ማረፊያውን በማድረግ አሁንም ከሀብታሞቹ ቀዳሚ ሶስት ተጫዋቾች መካከል ስሙን በ141 ሚሊየን ዶላር ገቢ በሶስተኝነት ማስፈር ችሏል፡፡ ሊዮኔል ሜሲ፤ በኑካምፕ አሁንም የእርሱን ያህል ገቢ ያለው ተጫዋች የለም፤ ተወዳጅ ነው፤ የማስታወቂያ አሰሪዎችም ከእርሱ ጋር አሁንም በልኩ ይሰራሉ፤ በ295 ሚሊየን ዶላር ንፁህ ገቢ ሁለተኛ ነው፡፡ አንደኛ ደረጃ ላይ ደግሞ በክፍያ ደረጃ ከሜሲ አነስተኛ ነው የሚከፈለው፤ እድሜው እየሄደ ቢሆንም ከማስታወቂያ ስራው የሚያገኘውን ግን አትጠይቁኝ፤ በወረፋ ነው ምርቶችን የሚሸጠው፤ ክፍያውም በዛው ልክ ከፍ ያለ ነው፡፡ በ321 ሚሊየን ዶላር ቀዳሚው ሀብታም ነው፤ ፖርቱጋላዊው የዩቬንቱስ ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ፡፡